በእሳት የተፈተነች ወርቅ!

አለም ዘመኗን በአባታዊ ስርዓት ስትቆጠር ኖራለች፡፡ ሴቶችን ያገለለ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስርአት በዓለም ላይ ተንሳራፍቶ ለበርካታ ዘመናት ቆይቷል፡፡ ለሴቷ እኩል እድል ተነፍጎል፤ የሴቷ አስተዋፆ በቤት ውስጥ ተገድቧል፡፡
በቤት ውስጥ የማይተካ ሚናን ብትጫወትም የኃላፊነት ሚናው፣ የመወሰን መብት ለወንዱ ተሰጥቷል፡፡ በሴቶች ላይ ያለውን ጫና ተቋቁማ መሰናክሎችን አልፋ ለአደባባይ የበቃች ሴት በተግባር እና በአመለካከት ጫና ሲደረግባት ሰንብቷል፡፡ ይህ ተግባር ይብቃ ያሉ ጀግኒቶች ለመብታቸው ትግል ጀመሩ ጀግና ወንድሞችም ተከተሏቸው፡፡ የሴት ልጅ መብት መከበር ሊያርቁት የማይቻል የጋራ ጥቅም ነውና ትግሉ ለሴቶች መብት ትግል መነሻና ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ ጅማሮ ሆነ፡፡
አለም የስርዓተ ፆታ እኩልነት ባለመከበሩ ከሴት ሙሉ አቅም መጠቀም የሚገባትን አስተዋፆ እንድታጣ ሆኗል፡፡ ሴቶች አሳታፊና እኩል እድል ባለማግኘታቸው እንዲሁም በአመለካከትና በተግባር የሚደርስባቸው ተፅኖ ከፍተኛ በመሆኑ አበርክቶዋቸው ገደብ ተጥሎበታል፡፡ አቅማቸው ታምቋል፡፡ የስርዓተ ፆታ እኩልነት ጉዳይ (ለውጦች ቢኖሩም) ዛሬም አለም ያልተሻገረው ችግር ነው፡፡ ከሀገር ሀገር የለውጥ ደረጃው ቢለያይም ልንመልሰው የሚገባ የመብት ጥያቄ ሆኖ ዘልቋል፡፡
ብዙ ተፅእኖዎችን ያለፈች፣ ኃላፊነቷን በብቃት የተወጣች ጀግኒት በሁሉም ዘርፍ አለች፡፡ ጀግኒት ለመሆን ጀግኒትን ለመፍጠር አቅሙ ያላት፡፡ ለብዙ ታዳጊዎች ምሳሌ የምትሆን በብዙ ጫና ውስጥ አልፋ ለሀገር፣ ለወገን፣ ለቤተሰብ የማይተካ ሚናን የተጫወተች እልፍ ጀግኒት አለች፡፡ ከወንድሟ እኩል ኃላፊነቷን ሀገሯ የምትጠብቅባት፡፡ ኃላፊነቷንም በአስገራሚ ሁኔታ የተወጣች… ከቤተሰብ እስከ ሀገር ግንባታ በአስተሳሰብ እና በተግባር የሚደርስባቸውን ተፅእኖ አሸንፈው ትልቅ አስተዋፆ ያበረከቱ እና እያበረከቱ ያሉ ታሪክ የሚያወሳቸው፣ ተግባራቸው ያልተመዘገበ አሻራቸውን ያኖሩ፣ በዛሬ ስራዎቻቸው የሚደነቁና ምሳሌ የሚሆኑ ጀግኒቶቻችን ነበሩ፣ አሉ፣ ወደፊትም ይኖራሉ፡፡ እነኝህ በእሳት የተፈተኑ ወርቆች ሊደነቁና፣ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ ከማድነቅና ከማመስገን ባለፈ የነገዋ ጀግኒት መሰናክሏን በማለፍ አላማዋን ከግብ ለማድረስ አራያቸውን ልትከተል ይገባል፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሴቶችን በተመለከተ በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና በባህል መስኮች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚነታቸው የተረጋገጠባት እና የሥርዓተ-ፆታ እኩልነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ራዕይ ሰንቆ እየሠራ ይገኛል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ የሴቶችን መብትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በአንድ አካል ብቻ የሚሰራ ባለመሆኑ ሁሉንም ባለቤት ባደረገ መልኩ እየሰራ ይገኛል፡፡
የሴተዋ ጉዳይ ለሴቷ ብቻ የማይተው ሁሉም የሚመለከተው በመሆኑ በጋራና በቅንጅት እየተሰራ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ሴቷ ለራሷ ጉዳይ ቀዳሚ ተሰላፊ እንድትሆን አርአያ የሚሆን ተግባርም በሚኒስቴር መስሪያቤቱ ከፍተኛ የስራ ኋላፊዎች ተንፀባርቋል፡፡ በሚኒስቴር መስሪያቤቱ ከፍተኛ የሥራ ኋላፊነት ደረጃም እኩል እድል ተመቻችቷል፡፡ በሚኒስትር፣ በሚኒስትር ዴኤታ ደረጃ ሴቶች የመሪነት ሚናቸውን ይዘው ሀገር የምትጠብቅባቸውን፤ መንግስት የጣለባቸውን ኋላፊነት እየተወጡ ይገኛል፡፡
ተፈጥሮ የቸረችንን ፀጋ ተቀብለን ልዩነታችንን ውበታችን አድረገን ሴቷ ለጉዳይዋ ቀድማ በመሰለፍ ወንዱም የእህቱ ጠበቂ በመሆን በጋራ ለመብቷ ሲታገል፤ የስርዓተ ፆታ እኩልነት ሜዳው ተገቢውን ቦታ ይይዛል፡፡ ጀግኒት የሆነችውና ሰርታ ጀግኒት ለመባል አቅሙ ያላት ሴት ዛሬም ሜዳው እኩል ሊያሳትፋትና እኩል የመወሰን መብትን ሊሰጣት ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ የተናጥል ትግል ውጤቱ የላላ ነውና ከአመለካከት እስከ ተግባር ለውጥ ለማምጣት በሥርዓተ ፆታ ዙሪያ ሁላችንም በጋራ ልንሰራ ይገባል፡፡ በሁሉም መስክ እኩል ተሳትፎ እንዲመቻች በጋራ እንስራ፡፡
መልካም የሴቶች ቀን!!
ቀናችንን ስናከብር አላማችንን ከግብ ለማድረስ፤ ከመሰናክላችን ለመጠንከር ቃላችንን በማደስ፤ ለልጆቻችን በፆታ እድል የማትነፍግ እኩል እድል የጋራ ሜዳ የምታቀርብ ኢትዮጵያን ለማውረስ በጋራ ጠንክረን ለመስራት እንነሳ፡፡
በተአምር ተ/ብርሃን
Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *