በሃገር ወዳድነት፣ እርስ በእርስ በመደጋገፍና ለሰላም በሚደረግ ሁለገብ ጥረት የማይታለፍ ችግር የለም

በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ አሻራቸው ካሳረፉ ሴቶች መካከል አገርን በማስተዳደር ከሚታወቁ ሴቶች ውስጥ ንግስት ሳባ ፣ ንግስት እሌኒ ፣ እቴጌ ምንትዋብ እቴጌ ጣይቱና እና ንግስት ዘውዲቱ ይገኝበታል፡፡
ለምሳሌ ከጣሊያን ጋር በተደረገ ግጭት እቴጌ ጣይቱ በውሳኔ አሰጣጥ በነበራቸው ድርሻና ያደርጉት የነበረው ትግል እጅግ ከፍተኛ ነበር ፡፡ እቴጌ ጣይቱ የጦር ስልት በመንደፍ ይታወቃሉ፡፡ ከጣሊያን ጋር በነበረው ድርድርም ወሳኝ ሚና ነበራቸው፡፡
ጀግናዋ እቴጌ ጣይቱ ለጥቁር ህዝብ ኩራት ለሆነው ለአድዋ ድል መገኘት ለአዲስ አበባ መቆርቆርና ለመሳሰሉት ኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊና ፖለቲካዊ አመራር ብቃት የነበራቸው ሴት ነበሩ፡፡ የተለያዩ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ እድገቶችን ለአገራችን በማስተዋወቅ ረገድም ብዙ ሰርተዋል፡፡
በአፄ ሀይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት በፓርላማው ውስጥ ብቸኛዋ ሴት ተመራጭ ወ/ሮ ስንዱ ገብሩ በወቅቱ ከነበሩት ባላባቶች ጋር በፓርላማ በመሰብሰብ ሀገራዊ ሁኔታዎች ላይ በጋራ መድረክ ሊመክሩ የቻሉ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ፈር ቀዳጅ ሴት ናቸው፡፡
በማህበራዊ ዘርፍም ክብርት ዶ/ር አበበች ጎበና በብዙዎች ዘንድ አፍሪካዊቷ ማዘር ትሬዛ ተብለው ይታወቃሉ፡፡ በርካታ ወላጅ አልባ ህፃናት በማሳደግ የሚታወቁት ወ/ሮ አበበች ጎበና በ1972 ዓ.ም ጀምሮ የመጀመሪያውን ብሩህ ተስፋ የልጆች መንደርና ህፃናት ማሳደጊያ በማቋቋምና ስያሜውን አበበች ጎበና የህፃናት ማሳደጊያና ት/ቤት በሚል በመቀየር በርካታ ወላጅ አልባ ህፃናትን እና የችግረኛ ቤተሰብ ህፃናትን በተቋምና ከተቋም ውጪ የረዱ ተምሳሌት እናት ናቸው፡፡
በሌላ በኩል በብሔራዊ አደጋ ስጋት በቅርቡ የ2013 -14 የበጎ ፈቃድ አምባሳደር ሆና የተሾመችው የትነበርሽ ንጉሴ – በአዲስ አበባ የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞችና ልማት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ስትሆን የአካል ጉዳተኞችና የሴት ልጆች ትምህርት መብቶች ተሟጋችነቷ ትታወቃለች ፡፡ እንዲሁም ከ20 በላይ የበጎ ፈቃድ ቡድኖች ውስጥ ከመሳተፍ ባሻገር የኢትዮጵያ ዓይነ ሥውራን ሴቶች ብሄራዊ ማህበርን በሊቀ መንበርነት ትመራለች።
‘አማራጭ የኖቤል ሽልማት’ (LIVELHOOD NOVEL AWARD) በመባል የሚታወቀው የሽልማት መርሃግብር ከ2017 ዓ.ም ተሸላሚዎች አንዷ ኢትዮጵያዊቷ የአካል ጉዳተኞች መብት ተሟጋች ሎሬት የትነበርሽ ንጉሴ ሽልማቱን ያገኘችው “የአካል ጉዳተኞች መብቶችን በማስተዋወቅና በማካተት፣ አቅማቸውን ሙሉ በሙሉ እንዲገነዘቡ በማስቻልና የህብረተሰቡን አስተሳሰብ በመቀየር ላከናወነችው አበረታች ስራ” ነው።
ለበርካታ የሃገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሃገር ዜጎች በተምሳሌትነቷ ተጠቃሽ የሆነችው ሎሬት የትነበርሽ ንጉሴ በላይት ፎር ዘ ወርልድ (Light for the world) በዓለም አቀፍ ደረጃ የሕግና የአካቶ ትምህርት ከፍተኛ አማካሪ ሆና በማገልገል ላይ ትገኛለች
በአንድ ወቅት ፕሬዘዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከኢቲቪ አራት ማዕዘን የሴቶች ተሳትፎን በሚመለከት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ” ሴቶችን በማብቃት ረገድ ብዙ መሰራት ያለባቸው ተግባራት እንዳሉ በጽኑ እንደሚያምኑና የተጀመሩትን በርካታ ጥረቶች ማያያዝ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡”
በዚህ መሰረት በውጤቱም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለመድረስ በዩንቨርስቲዎቻችን ላይ በማተኮር ሴቶች በብቃትና በብዛት ተመርቀው እንዲወጡ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህን ስናሳካ ደግሞ በሙያቸው ስራ ገበያ ላይ ይገኛሉ – ከፍተኛ ሃላፊነት ቦታዎች ላይ ለመምጣት ይችላሉ – ለሹመትም ይበቃሉ – በዚህም የበቁ ሴቶች የሉንም ከሚለው አስተሳሰብ እንወጣለን፡፡” ማለታቸው አይዘነጋም ፡፡
ይህን መልካም ውጥን ከዳር ለማድረስ በቅርቡ በክብርት ፕሬዘዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አነሳሽነት የተጀመረውና በሃገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ተተኪ ሴት አመራሮችን ለማብቃት በአፍሪካ የአመራር ማዕከል የተዘጋጀው አቅም ግንባታ ስልጠና የሴቶችን የአመራርና ውሳኔ ሰጪነት ሚና በማጎልበትና ተተኪ አመራሮችን ለማፍራት በመንግስት በኩል ያለውን ፖለቲካዊ ቁርጠኝነትና ለሴቶች የተሰጠውን ልዩ ትኩረት ያሳያል፡፡
የዘንድሮው አለም አቀፍ የሴቶች ቀን በሀገራችን በተከሰተው ጦርንትና ግጭት ምክንያት ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በተለየ መልኩ ለፆታዊ ጥቃትና ለተለያዩ ችግሮች በከፋ መልኩ ተጋላጭ ለሆኑና ለተጎዱ ሴቶችና ህፃናት ድጋፍ ለማድረግና የተሻለ አፈፃጸም ያላቸውን እውቅና በመስጠት የሚከበር ይሆናል፡፡
የዘንድሮው ማርች 8 በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ111ኛ ጊዜ “Gender equality today for a sustainable tomorrow!” “የስርዓተ ፆታ እኩልነት ለዘላቂ ልማት!” በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ46ኛ “እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ!” በሚል መሪ ቃል ይከበራል፡፡
በዚህ መሰረት የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚሰሩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች የበለጠ ትኩረት እንዲያገኙ ከማድረግ ባሻገር አለም አቀፍ የሴቶችን ቀን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው ሃገር አቀፍ ንቅናቄ የድርጊት መርሃ ግብር ከየካቲት 1 እስከ መጋቢት 18 ቀን 2014 ዓ.ም በማህበራዊ ጉዳይ በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ አደጋዎች ተጎጂ የሆኑ ሴቶች እና ህፃናት ሁለንተናዊ ድጋፎችን እንዲያገኙ የሀብት ማሰባሰብ ተግባር በመስራት በዘላቂነት ከችግር እንዲወጡ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
ችግር ለደረሰባቸው ሴቶችና ህፃናት የስነ-ልቦና ድጋፍ አገልግሎት /psycho-social training / በመስጠት ወደ ቀድሞ ህይወታቸው እንዲመለሱ ከማድረግ በተጓዳኝ ጥቃት የደረሳባችው ሴቶች ምላሽ አሰጣጥና አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን የማጠናከር ስራ በመሰራት ላይ ነው፡፡
በተጨማሪም በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በሚዲያና የተለያዩ የግንኙነት ዘዴዎችን በመጠቀም የሴቶች ህብረት ስራ ማህበራት ማጠናከርና የተሻለ አፈፃፀም ያላቸውን ማህበራት እውቅና መስጠት ያስችላል፡፡
ሃገር አቀፍ ንቅናቄው የሴት አደረጃጀቶችና የልማት ቡድኖችን የበለጠ ለማጠናከርና ለማቋቋም እድል ከመፍጠር ባሻገር የሴቶች ልማት ቡድን ለአካባቢያቸው ሰላም ግንባታና ለብሄራዊ መግባባት ጉልህ ሚና እንዲጫወቱ ማድረግ ያስችላል፡፡
በዚህ መሰረት በሃገር ወዳድነት፣ እርስ በእርስ በመደጋገፍና ለሰላም በሚደረግ ሁለገብ ጥረት የማይታለፍ ችግር አለመኖሩን በመገንዘብ ህብረተሰቡ ፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሃይማኖት ተቋማት ፣ የንግዱ ማህበረሰብ አባላትና የባለሃብቶች በባለቤትነትና በቅንጅት በመስራት በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ለተጋለጡ ወገኖቻችን የጋራ የሆነ ፈጣን ምላሽ እንድንሰጥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጥሪ ያቀርባል፡፡
በዓለማየሁ ማሞ
Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *