ነጋችንን በተስፋ ማየት

ተስፋ ምንድን ነው? ለዚህ ጥያቄ ሰዎች እንደእምነታቸውና እውቀታቸው የተለያዩ መልሶች ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ ከዚህ ጽሁፍ ጋር በተያያዘ ተስፋ ወደፊት ስለሚሆነው ነገር በራስ የመተማመን ስሜት ወይም የምንፈልገውን የተሻለ ለውጥ የሚገልጽ ነው፡፡ ይህ ማለት የነገ ተስፋችን በዛሬ መስራት ውስጥ ይወሰናል፡፡
ከዚህ በመነሳት ነገ ከዛሬ የተሻለ ነው ወይም ከዛሬ የባሰ የሰቆቃና የመከራ ጊዜም ሊሆን ይችላል፤ ይህ በእኛ የዛሬ ተግባር የሚወሰን ይሆናል፡፡ ስለዚህ ነገን በተስፋ ለማየት እንደ ግለሰብ፣ እንደ ማህበረሰብና እንደ ሀገር ዛሬ ላይ ምን እየሰራን ነው? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡
በሀገራችን ኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታው በመዳህ ላይ ያለ በመሆኑ የስልጣን ሽግግሩ በ21ኛው ክ/ዘመን ስልጣንን እንደ እርስትና ጉልት በሚመለከቱ ጥቂት ግለሰቦች ምክንያት የእርስ በእርስ ጦርነት በማስከተሉ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት፤ የዜጎች ከቀያቸው መፈናቀልና ለተረጅነት መዳረግ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ በደቡብ እና በምስራቁ የሀገራችን ክፍል የተከሰተው ድርቅ የውሃ ማማ ተብላ በምትጠራ ሀገር ውስጥ እንስሳት ለእልቂት ተዳረገው አይተናል፤ ህዝቡም ለረሃብ ተጋልጧል፡፡ አሁንም ችግሩ እንደቀጠለ ነው፡፡
የነገዋን ኢትዮጵያ በተስፋ ለማየት እንደ ሀገር ዛሬ ተግባራችን ምን ይሁን ብለን መጠየቅ፣የያዝነውን እቅድና ተግባር መፈተሸ፣እርስ በርስ የሚያከራክሩ ጉዳዮችን መለየትና መፍትሔ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡
ዛሬን በትላንት መግደል ሳይሆን በነገ ተስፋ ማዳን ተገቢ ነው፡፡ በዛሬ እንዳይሰራና በልማት ላይ እንዳይተኮር፣ ጊዜ ጉልበትና ሀብት ለክርክር እየዋለና ለእርስ በእርስ ግጭት እየዳረገን ያለው እንደ እኔ አረዳድ የሀገራችን ፖለቲካ በታሪክና ዘውግ ላይ የተንጠለጠለ መሆኑ ነው፡፡ ታሪክ ትላንት ነው፡፡ ያለፈ ነው፡፡ ያለፈው ስርዓት ደግሞ ጥሩም መጥፎም ጎኖች ይኖሩታል፡፡ ጥሩም መጥፎውም ቅድመ አያቶቻችን ያወረሱን፣ እኛም የሰራነው ታሪካችን ነው፡፡ በታሪክነቱ እንይዘዋለን፤ ዛሬም ወደፊትም መጥፎው እንዳይደገም ከታሪክ ትምህርት ይወሰድበታል እንጂ ሌላ ትርጉም ሊሰጠው አይገባም፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ሊሂቃኑ ታሪክን በዘውግ መነፀር እያዩና እየተረጎሙ የማህበረሰቡን የአብሮነት የመደጋገፍና የአንድነት እሴቱን ከመሸርሸርና ነገን የምንሰራበትን ጊዜ ጉልበትና ሀብት ከማባከን መቆጠብ ይኖርባቸዋል፡፡
ሌላው የንትርክ ምክንያት በዘውግ ላይ ያተኮረ የፖለቲካ ስርዓት መከተላችን ነው፡፡ ሀገራችን የብዙ ቋንቋዎችና እምነቶች ባለቤት ናት፡፡ ታዲያ እንዴት ፈጣሪ የሰጠን የቋንቋና የእምነት ፀጋ ለንትርክና ግጭት ሊዳርገን ይችላል? በሚሊዎን የሚቆጠሩ ቤተ እምነቶች ባሏትና ዜጎቿ ባለእምነት ናቸው በምትባል ሀገር እርስ በእርስ የመተማመን እሴታችን ማን ወሰደብን? በጊዜ ሂደት በሰው ልጅ አዕምሮ ከተፈጠረው ውጪ ፈጣሪ በዘውግ/በብሔር አልፈጠረንም፤ በአምሳሉ ሰው አድርጎ እንጂ፡፡ የፖለቲካ ስርዓቱ ዘውግን/ብሔርን ማዕከል ያደረገ በመሆኑ ውድድራችን እርስ በርስ ሆኗል፤ የትኛው ዘውግ የተሻለ ስልጣን አገኘ ነው እንጂ የህዝቡ የኑሮ መሻሻል የውይይት አጀንዳ እየሆነ አይደለም፡፡ ዓለማችን የደረሰችበት ሳይንስና ፈጠራ ተዘንግቷል፤ ወጣቶች ከሳይንስና ምርምር ይልቅ የፖለቲካው አዳማቂና መስዋዕት ከፋይ እንዲሆኑ እየተደረገ ዛሬን ደርሰናል፡፡ ከዚህ ላይ ፖለቲካው በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ላይ ዳፋው ከፍ ያለ መሆኑን ልብ ልንለው ያስፈልጋል፡፡
ስለዚህ የነገን የኢትዮጵያ ተስፋ ለማየት ዛሬን መስራት ይገባል፡፡ የዜጎችን እኩልነትንና ፍትሐዊነትን የሚያነግስ የፖለቲካ ስርዓት መትከል፣ ህግና ስርዓት ማስጠበቅ፣ ልዩነት ከውበትም በላይ የሀብት ምንጭ እንደሆነ በመገንዘብ ቋንቋዎችና እምነቶች እንዲያድጉና በቱሪዝም የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ ዛሬን መስራት ይጠይቃል፤ ከፖለቲካ ትኩሳቱ በመውጣት የኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግና ሜጋ ፕሮጀክቶችን በማቀድና በማልማት የህዝቡን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል ይገባል፡፡ ውድድራችን ከእርስ በእርስ ወጥቶ እንደ ሀገር በዓለም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ልህቀቶች ላይ ማተኮር አለበት፡፡ ዜጎች ለሀገር ልማት የበለጠ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደረጉ ማስተባበርና ማበረታታት፣ ወጣቶች አሁን ካለው ጅምላ አስተሳስብ ወጥተው በትምህርትና ስልጠና ሳይንስና ፈጠራ ላይ እንዲያተኩሩ መደገፍ ይኖርብናል፡፡ ይህ ሲሆን ዛሬ ላይ ልማታችን የተፋጠነ፣ ከድህነትና ከተረጂነት የምንላቀቅበት ጊዜም አጭር፣ ዜጎች ባለጤና፣ ነጋችን ብሩህ በተስፋ የተሞላ ይሆናል፡፡
Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *