የዘንድሮ የ16ቱ የፀረ-ፆታ ጥቃት ቀናትን አከባበር ማስጀመሪያ መረሃ ግብር ተካሄደ

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፕሬዝዳነት ክብርት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘዉዴ መረሃ ግብሩን በመክፈቻ ንግግር ሲከፍቱ እንደገለፁት የሴቶችን መብት ለማስከበር 365 ቀንና የ 24 ሰዓት ስራችን መድረግ አለብን፡፡ ከመፈክር ወጥተን መፈክር ወደ መሬት የሚወርድበትን መሰላል ማዘጋጀት ይጠበቅብናል፡፡ ባለፈው ክፍለ ዘመን ያልፈታነው ችግር ነው በ21ኛው ክፍለ ዘመን በመጎተት ሴቶች ላይ ጫና የሚያደርሰዉ የሴቶች እኩልነት፤ መብትና ደህንነት ሊከበር የሚችለዉ ተጨባጭ፤ መሬት የወረዱ የሆኑና የይስሙላ ያልሆኑ እርምጃዎች ሲወሰዱ ነው፡፡ 16ቱን ቀን ሁላችንም ታጥቀን እንዝመት ብለዋል፡፡

ክብርት ፕሬዝዳንቷ አክለዉም በብዙ ሃገር የሚታየው በኛ ሃገርም በቅርብ ጊዜ ትዝታና አሁን ያለንበት ችግር የሆነው የሰቆቃ ምልክት ሴት መልክና ሴቶች ናቸዉ፡፡ የህብረተሰብ ጉዳት መለያ ምልክት ሴት ነች፡፡ አሁንም በጦርነት በተፈጠረው ቀውስ ከተማ በተጎዳ ቁጥር ከመጠለያ ወደ ሌላ መጠለያ ልጅ አዝለዉ ፤የተለያዩ የቤተሰብ ጫና በመሸከም ርጅም ኪሎሜትሮችን በስደት ሲጓዙና ሲንገላቱ የምናያቸው ሴቶችና ህፃናት ናቸው፡፡ ነገር ግን ሴቶች የሰቆቃ ምልክት ብቻ አይደሉም ሴቶች የመፍትሄ አካል ናቸዉ፡፡ ሴቶች የመፍትሄ አካል ካልሆኑ ጎዶሎ መፍትሄ ነው የሚሆነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በማለት ገልፀዋል፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በፕሮግረሙ ላይ እንደገለፁት የኢፌ.ዴ.ሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በአለም ለ30ኛ ጊዜ በአገራችን ደግሞ ለ16ኛ ጊዜ የዘንድሮ የፀረ-ፆታዊ ጥቃት ቀን “ሰላም ይስፈን፤ በሴቶንና ህጻናት ላይ የሚደርስ ጥቃት ይቁም!” በሚል መሪ ቃል በብሔራዊ ደረጃ ከህዳር 16 – ህዳር 30 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ለ16 ተከታታይ ቀናት የህብረተሰቡን አመለካከት ለመለወጥና ድርጊቱን ለማስቆም በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አጽዕኖት ሰጥቶ ለማስገንዘብ ያለሙ የንቅናቄ ስራዎችን እንዲካሄዱ በቅንጅት እየሰራ ይገኛል፡፡ ብለዋል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ 16ቱን ቀናት አዳራሽ ውስጥ ከማክበር በዘለለ በተለይ በጸጥታ ችግር ምክንያት ለተፈናቀሉ ሴቶችና ህጻናት እንዲሁም የአንድ መስኮት እና የማገገሚያ አገልግሎት ለሚሰጡ ማዕከላት ድጋፍ ለማድረግ እንዲያስችል ከህዳር 16 – 25 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ “የእህቴ ጠባቂ ነኝ” ወይም `I Care for MY Sister` በሚል መሪ ቃል ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ከግል ባለሃብቶች፣ ከሲቪል ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ደረቅ ምግቦች፣ የዱቄት ወተት፣ ዘይት፣ የንጽህና መጠበቂያና የማብሰያ ቁሳቁሶች፣ የተለያዩ ልብሶች፣ ብርድ ልብሶች፣ አንሶላዎች፣ ፍራሶችና የመሳሰሉትን ግብዓቶች ለማሰባሰብ እቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በመድረኩ ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤የጤና ሚኒስቴር፤የፈትህ ሚኒስቴር ፤ የፌዴራል ፖሊስ ኮምሽን፤የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮምሽን፤ የሲቪል ማህብረሰብ ድርጅት እዲሁም ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የበላይ አማራር የተሳተፉበት የሴቶችን ጥቃት መከላከልና ማስቆም ላይ ያተኮረ የፓናል የውይይት መድረክ ተካሄዷል፡፡

የ16ቱ ቀን የፀረ-ፆታዊ ጥቃት ቀን እንዲከበር መነሻ የሆነው በካናዳ ሞንትሪ ኢንጂነሪንግ ት/ቤት ውስጥ “አክራሪ የሴት እንቅስቃሴ መሪዎች” በሚል በአንድ ወንድ የተገደሉትን 14 ሴቶችና ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚሞቱ ሴቶችን ለማስታዋስ ነው፡፡በሌላ በኩል ቀኑ ህዳር 16 /ኖቬምበር 25 / እንዲከበር የተደረገው በ196ዐ በአምባገነኑ የዶክሚኒካን ሪፐብሊክ መሪ ራፋኤል ትሩጂሎ የተገደሉትን የሚራባል እህትማማቾችን /Mirabel Sisters/ ለመዘከር እንደሆነ አንዳንድ ፅሁፎች ያትታሉ፡፡ እነሆ በአሉ በአለም አቀፍ ደረጃ እ.አ.አ ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ ቀናቱ በተለያዩ መሪ ቃሎች ሲከበር ቆይቷል፡፡

Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *