የሴቶች የልማት ቡድን የአደረጃጀትና አሰራር ማንዋል ለማሻሻል የምክክር መድረክ ተካሄደ

(ጥር 24/2015 ዓ.ም አዲስ አበባ) አገር አቀፍ የሴቶች የልማት ቡድን የአደረጃጀትና አሰራር ማንዋል ለማሻሻልና ግብዓት ለማሰባሰብ ከፌዴራል ስትሪንግ ኮሚቴ አመራሮች ጋር የምክክር መድረክ ተካሄደ።
የኢ.ፌ.ድ.ሪ. የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶች ማብቃት መሪ ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ወይንሸት ገለሶ በመክፈቻ ንግግራቸው የሀገራችን ሴቶች ችግሮቻቸው ከተቀረፉላቸው፣ መብቶቻቸው ከተከበሩላቸው፣ በንቃታ መሳተፍ የሚችሉበት ምቹ መደላደል ከተፈጠረላቸውና አቅም በፈቀደ መጠን ከደገፍናቸውና ጥረታቸውን ካበረታታናቸው የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ህይወት ከመለወጥ ባለፈ ለማህበረሰብ ለውጥ እና ለሀገር ብልጽግና ጉለህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ገልጸዋል።
ሴቶች ህገ መንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው በተለያዩ ዘርፎች መደራጀት በመቻላቸው ቀደም ባሉት ጊዜያት ተግባራዊ በሆነባቸው የታችኛው መዋቅር ይደርስባቸው የነበሩ ችግሮችን በጋራ በመንቀሳቀስ የጋራ መፍትሔ እየሰጡ በሄዱበት አግባብ አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻላቸው ይታወቃል ሆኖም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የአደረጃጀቱ እንቅስቃሴ በሁሉም አካባቢዎች በሚባል ደረጃ እየተቀዛቀዘና እየተዳከመ መምጣቱን ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን በተለያዩ ጊዜያት ባካሄደው የዳሰሳ ጥናት ውጤት ለመገንዘብ ተችሏል ብለዋል።
አክለውም ማኑዋሉ ለሴት አደረጃጀቶችም ሆነ እንደሀገር በየመስኩ ለነደፍናቸው የልማት ውጥኖችን ከዳር ለማድረስ የሚደረገውን ሁለንተናዊ ጥረት ማሳካት የሚያስችል ጠንካራና የተደራጀ ሀይል በመፍጠር ረገድ የሚኖረውን ጉልህ ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት ከዝግጅት እስከ ትግበራ ምዕራፍ ያለውን ሂደት በመከታተል፣ በመደገፍና በማጠናከር በኩል ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ከባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚኖርበት ገልጸዋል።
የምክክር መድረኩም ለሁለት ተከታታይ ቀናት ተካሄደ ሲሆን የሴቶች ልማት ቡድን የአደረጃጀት ማንዋልና የሴቶች አደረጃጀቶችና ባለ ድርሻ አካላት የተጠናከረ የመረጃና የግንኙነት አግባብ ስርዓት ለመዘርጋት የተዘጋጀ የማእቀፍ የጹሁፍ ሰነድ ቀርቦ የልማት ቡድን የአደረጃጀትና የአሰራር ማኑዋል ለማሻሻል የሚረዱ ግብዓቶችን በመስጠት ሰፊ ውይይት ማድረግ ተችሏል።
በመጨረሻም የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶች ማብቃት መሪ ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ወይንሸት ገለሶ የተሰተው ግብዓት ጠቃሚና አስፈላጊ መሆኑን አንስተው እዚህ የተገኘነው አካላትም ምን ብናደርግ ውጤት ማምጣት እንችላለን የምንችልበትን ስራ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *