የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት በይፋ ተመሠረተ

(አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24/2015 ዓ.ም) በሀገራችን ታሪክ የመጀመሪያ የሆነው የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ለወጣቶች ድምፅ በሚል መሪ ቃል በዛሬው ዕለት በስካይላይት ሆቴል በተካሄደ ደማቅ ስነስርዓት በይፋ ተመሠረተ።

በምስረታ ስነስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ባስተላለፉት መልዕክት እንደተናገሩት፤ ምክር ቤቱ መመስረቱ የወጣቶችን ችግር ለመቅረፍ ብሎም ለሀገረ መንግስት ግንባታ እንደሀገር ለሚደረገው ሁለንተናዊ ጥረት ስኬታማነት ጉልህ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

በመሆኑም ምክር ቤቱ የተቋቋመለትን ዓላማ እንዲያሳካ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቅንጅት ይሰራል፤ የበኩሉንም እገዛና ድጋፍ ያደርጋልም ብለዋል።

ምክር ቤቱ በቀጣይ ለወጣቶች መብትና ጥቅም መከበር እንዲሁም ለዘላቂ ተሳትፎና ተጠቃሚነት መላው አባላቱን ማንቀሳቀስ ይጠበቅበታል ያሉት ሚኒስትሯ ርዕይው ይሳካ ዘንድም ከሚመለከታቸው ባለድርሻና አጋር አካላት ጋር እየተመካከረ በቅርበት ሊሰራ እንደሚገባ በአፅዕኖት አሳስበዋል።

ምክር ቤቱ መመስረቱን በይፋ ያበሰሩት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የትራንስፓርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ሚኒስትር እና የዕለቱ የክብር እንግዳ ክቡር ዶ/ር አለሙ ስሜ በበኩላቸው ወጣቶች በርካታ ችግሮች ያሉባቸው እንደመሆኑ ችግሮቻቸው ከመፍታት አኳያ ምክር ቤቱ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት መወጣት እንዲችል አደረጃጀቱን በሚገባ ማጠናከርና መደገፍ እንደሚገባ ገልፀዋል።

ለምክር ቤቱ አባላትና ስራ አስፈፃሚዎችም መልካም የስራ ዘመን እንዲሆን ዶ/ር አለሙ ከልብ ተመኝተዋል።

ለመላው የኢትዮጵያ ወጣቶች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፈው የምክር ቤቱ ፕሬዝደንት ወጣት ፉአድ ገና ምክር ቤቱ በወጣቶች ላይ ትኩረት ያደረጉና ወጣቶች ለሀገር ሰላምና ብልፅግና የሚኖራቸውን አበርክቶ ይበልጥ ለማጎልበት የሚያግዙ በርካታ ተግባራትን ለማከናወን ማቀዱን አስታውቋል።

ስለሆነም ለስኬታማነቱ መላው የምክር ቤቱ አባላትና ስራ አስፈፃሚዎች በመቀናጀት በቁርጠኝነት፣ በላቀ ትጋትና ተነሳሽነት እንደሚሰሩና ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግሯል።የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ከምክር ቤቱ ጎን እንዲቆሙና ድጋፋቸውንም እንዲያጠናክሩ ወጣት ፉአድ ጥሪ አቅርቧል።

በዕለቱ የሚኒስትር መ/ቤቱ የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሙና አህመድ የምክር ቤቱ አባላትና ስራ አስፈፃሚዎችን ቃለ መሀላ አስፈፅመዋል።

በስነስርዓቱ ላይ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ ወጣቶች፣ የወጣት አደረጃጀቶች፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ተቋማት ተወካዮች፣ የሚዲያ አካላትና ሌሎችም ተገኝተዋል፤ አዝናኝ ዝግጅቶችም ቀርበዋል።

 

Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *