አዳዲስ የቢዝነስ ሃሳብ ያላቸውንና የኮምፕዩተር ሳይንስ እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምሩቃን ሴቶችን የስራ ፈጠራ ወደ ገበያ ለማስገባት እንዲያስችል በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ ውይይት ተካሄደ

 

(አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25/ 2015 ዓ.ም) መድረኩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዩ ኮድ ገርልስ (UCode girls) ከተባለ አጋር ድርጅት ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን ፕሮግራሙ በዋነኝነት ከቴክኖሎጂና ስራ ፈጠራ ጋር በተያያዘ የክህሎት፣ የአመለካከትና የባህሪ ለውጥ ለማምጣት የሚያግዙ ስልጠናዎችን በመስጠትና ልዩ ልዩ ድጋፎችን በማድረግ ስራ ፈጣሪ ሴቶችን የተሻለ ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ በቅንጅት መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመምከር ያለመ እንደሆነ ተገልፇል።

በውይይቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢፌ.ዴ.ሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደተናገሩት፤ ዘመኑ የቴክኖሎጂና የኢንፎርሜሽን የቴክኖሎጂ ውጤት አማራጮች በብዛትና በፍጥነት ከአምራች ወደ ተጠቃሚው እየቀረበ ያለበት ወቅት መሆኑንና ይህም በዕለት ተዕለት ስራችንና የአኗኗር ዘይቤያችን ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

በቴክኖሎጂው አቅርቦት፣ በመሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ በተደራሽነትና በአጠቃቀም ረገድ በተለይ ልጃገረዶችና ሴቶች ላይ እንዲሁም በከተማና በገጠር ሰፊ ክፍተትና ልዩነት መኖሩንም አንስተዋል።

ለአብነትም በየደረጃው ባሉ የትምህርት ተቋማት ሳይቀር ልጃገረዶችና ሴቶች በቴክኖሎጂ መስክ ያላቸው ተሳትፎ አናሳ መሆኑንና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም በዘርፉ ከተመረቁ ሴቶች መካከል 42 በመቶ ያህሉ ብቻ የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።

በመሆኑም መንግስት የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ ፕሮግራሞች ተነድፈው በትምህርት ሚኒስቴር፣ በኢንሳ፣ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እቅድ ውስጥ ተካትቶ እየተገበረ መሆኑንና የተለያዩ አጋር አካላትም የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ጅማሮዎቹ ውጤታማ እንዲሆኑና ሴቶችን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ የማስተባበርና የመደገፍ ሚናውን ለመወጣት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የዩኮድ ገርልስ (UCode girls) መስራችና ኢትዮጵያዊቷ የሶፍትዌር ኢንጂነር ዶ/ር ቤተልሄም ግሩንበርግ በበኩላቸው ድርጅታቸው በኢትዮጵያ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና በስራ ፈጠራ መካከል ያለውን የስርዓተ ፆታ ክፍተት ለማጥበብ የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ያለመ ፕሮግራም ይዞ መቅረቡን አስረድተዋል።

ፕሮግራሙ በጥናት ላይ በመመርኮዝ በተለያዩ ክልሎች በከፍተኛ የመንግስት የትምህርት ተቋማት እና በቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩትዎች ውስጥ በመማር ላይ በሚገኙና ምሩቃን ሴት ተማሪዎች ላይ ለማስጀመርና በቀጣይ ውጤቱ እየታየ ለማስፋት መታቀዱንም ገልፀዋል።

Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *