የኢትዮጵያ ዕድሮች ጥምረት ምክር ቤት የመጀመሪያ መደበኛ ስብሰባውን አካሄደ

(አዳማ፣ መጋቢት 26/2015 ዓ.ም) የኢትዮጵያ ዕድሮች ጥምረት ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ የመጀመሪያ መደበኛ ስብሰባውን አካሄደ፡፡
ምክር ቤቱ በክሎችና በጥምረቱ አማካኝነት ከምስረታ በኃላ በማህበራዊ፣ በጤናና በሌሎችም ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራት፣ በቀጣይ እቅዶችና የትኩረት አቅጣጫዎች ላይም ሰፊ ውይይት አካሂደዋል፡፡ በተመሳሳይ በመተዳደሪ ደንቡ ላይ ሊደረጉ በሚገቡ ማሻሻያዎች ዙሪያም ውይይት ተካሂዷል፡፡


በስበሰባ መድረኩ ላይ የተገኙት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ ዕድሮች የሞተን ከመቅበርና ያዘነን ከማጽናናት የተለመደ ተግባር በዘለለ እንደየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ፕሮጀክት በመቅረጽ የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት የሚያስችሉ ማህበረሰብ አቀፍ ድጋፎችን በማድረግ ረገድ ያላቸው ሚና እጅግ የላቀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለዚህም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በመተባበር በተደረገ ሰፊ ጥረት በሀገር አቀፍ ደረጃ የዕድሮች ጥምረት ምክር ቤት መቋቋሙን አስታውሰዋል፡፡
በመሆኑ በመተባበር የማይናድ የችግር ተራራ፣ በመተጋገዝ የማይነቀል የችግር ደንቃራ፣ ተቀናጅቶ በመስራት የማይራገፍ የችግር አቧራ የለምና ዕድሮቻችንና ጥምረቶቻቸው ዘመን ተሻጋሪ የሆነውን የመረዳዳት ባህል ይበልጥ በማጉላት ያላቸውን እምቅ አቅም፣ ልምድና ተሞክሮ እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ እየተፈጠረ ያለውን ምቹ ሁኔታ አሟጠው በመጠቀም ለሀገር ሠላምና ዕድገት መፋጠን፣ ለማህበራዊ ትብበር መጎልበትና የህብረተሰቡን ችግሮች የመቅረፍ የጀመሩትን ጥረት የበለጠ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ሚኒስትር ዴኤታዋ ወ/ሮ አየለች እሸቴ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በ2007 ዓ.ም ፀድቆ በሥራ ላይ የዋለውን ብሔራዊ የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ የትኩረት አቅጣጫ መሰረት በማድረግ በህብረተሰቡ ውስጥ በተለያዩ ችግሮችና አደጋዎች ምክንያት የሚፈጠሩ ጫናዎችን ለማቃለል ብሎም የሀገርን ሠላምና ልማት እውን ለማድረግ የኢትዮጵያ የዕድሮች ጥምረት ምክር ቤት ያስቀመጠው ግብ እንዲሳካ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል፡፡

Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *