ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አካል ጉዳተኞች ለሚማሩባቸው ትምህርት ቤቶች ዘጠኝ መቶ ሺህ ብር የሚገመት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች መሪ ስራ አስፈጻሚ በወላይታ ሶዶና በሰበታ አይነ ስውራን
ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በሆሳዕና መስማት የተሳናቸው ትምህርት ቤቶች በመገኘት ባደረገው ምልከታ ለተማሪዎቹ
አስፈላጊ የሆኑና ዋጋቸው ዘጠኝ መቶ ሺህ ብር የሚገመቱ የትምህርት ቁሳቁሶችን ለየትምህርት ቤቶቹ የስራ ሃላፊዎችና
ተወካዮች አስረክቧል ፡፡
በርክክቡ ላይ የተገኙት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የማህበራዊ ጉዳዮች ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴ
እንደገለጹት የአካል ጉዳተኞች ዘላቂ ተጠቃሚነት ጉዳይ በ10 ዓመቱ የተቋሙ መሪ እቅድ ውስጥ ትኩረት የተሰጠውና
ከየክልሉ ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮዎች ጋር በመቀናጀት የሚከናወን ተግባር ነው፡፡


በዚህ መሰረት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት እየተሰራ ያለው የአካቶ ትምህርት ልዩ ተጠቃሽ መሆኑን የገለጹት
ሚኒስትር ዴኤታዋ በቀጣይም ከኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽንና ከብሔራዊ ማህበራት ጋር በመቀናጀት
አካል ጉዳተኞች የሚማሩባቸውን ት/ቤቶች በአካባቢያቸው ከሚገኙ ዩንቨርሲቲዎች ጋር በማስተሳሰር የአካል
ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንተጋለን ብለዋል፡፡
የሆሳዕና መስማት የተሳናቸው ትምህርት ቤት የስራ ሃላፊ አቶ ታደሰ ገዕኖሬ በሰጡት አስተያየት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ
ቀደም ሲል በትምህርት ቤቱ ባለሙያዎችን በመላክ ባደረገው ምልከታ መሰረት ያሉብንን ችግሮች በመረዳትና ቅድሚያ
ሊሰጠው የሚገባውን በጣም አስፈላጊ ድጋፍ በመለየት ለተደረገላቸው ድጋፍ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡
ድጋፍ ከተደረጉ የትምህርት ቁሳቁሶች መካከል የብሬይል ወረቀት፣ ስሌት እና ስታይለስ ፣የድምጽ መቅጃ ሪከርደርና ነጭ
በትሮቹ ለወላይታ ሶዶና ለሰበታ አይነስውራን ት/ቤቶች የተሰጡ ሲሆን የጆሮ ማዳመጫዎቹ ደግሞ በሆሳዕና መስማት
የተሳናቸው ትምህርት ቤት ለሚማሩ ተማሪዎች የተበረከተ ነው፡፡

Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *