የጸረ አደንዛዥ ዕፆች አገር አቀፍ ንቅናቄ በዛሬው ዕለት በይፋ ተጀምሯል።

(አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4/2015) የጸረ አደንዛዥ ዕፆች አገር አቀፍ ንቅናቄ መርሀ ግብር የፌዴራል፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር የቢሮ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርስቲ ተወካዮች፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የወጣቶች ምክር ቤት አመራሮችና ሌሎች በጉዳዩ ላይ የሚሰሩ አካላት በተገኙበት በይፋ ተጀምሯል።

የንቅናቄ መድረኩን ያስከፈቱት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ አገራችን የወጣቶች አገር ናት፤ ወጣቶች ያላቸውን ዕምቅ አቅም በመጠቀም ዘላቂ ልማትና ሰላም ለማረጋገጥ ለወጣቶቿ የምትሰጠው ትኩረት ወሳኝ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም በከተሜነትና በሉዓላዊነት ምክንያት በመጤ ባህሎችና አደንዛዥ ዕፆች ተጠቃሚነት በወጣቶችና ታዳጊዎች ስብዕና ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

‘ብንዘገይም አረፈደብንም’ ያሉት ሚኒስትሯ የወጣቶችና ታዳጊዎችን ስብዕና በመገንባት በራሳቸው ባህል የሚኮሩ፣ አገራቸውን የሚወዱ፣ ጤናማና አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ከቤተሰብ ጀምሮ ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻና አጋር አካላት ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ በአፅዕኖት አሳስበዋል።

የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሙና አህመድ በበኩላቸው ትልቅ የፈጠራ አቅምና ተነሳሽነት ያለው ወጣት ትውልድ በዕጽና መጤ ልማድ ምክንያት ከመንገድ ሊቀር አይገባም ብለዋል።

የንቅናቄ ፕሮግራሙ ትውልድ የማዳን ጉዳይ በመሆኑ ውጤት ሊያመጣ በሚችል፣ በተቀናጀ አግባብ ወጣቱንም ጭምር የመፍትሄው አካል አድርገን መረባረብ ይጠበቅብናል ሲሉ ተናግረዋል።

በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ማብቃት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ባንቹ ሙሉጌታ የአገራዊ ንቅናዌውን መነሻ ዕቅድ አቅርበዋል።

እንደስራ አስፈፃሚዋ፤ አገራዊ የፀረ አደንዛዥ ዕፆች ንቅናቄ በቀጣይ አንድ ዓመት የሚተገበር ሲሆን መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት ትብብር የወጣቶችን ስብዕና ለመገንባት ርብርብ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

“ወጣቶችን ከአደንዛዥ እፅችና ከአሉታዊ መጤ ልማዳዊ ድርጊቶች እንታደግ” በሚል መሪ ቃል በተጀመረው የንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ ጥቁር አንበሳ ህክምና ትምህርት ቤት የአዕምሮ ህክምና መምህር ፕሮፌሰር ሰለሞን ተፈራ አደንዛዥ እፅ በወጣቶች ስብዕናና በህይወታቸው ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተፅዕኖ በሚል ርዕስ ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቧል።

በቀረቡ ሰነዶች እና የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት በማካሄድ የጋራ መግባባት ተደርሷል።

Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *