የ2015 የትንሳዔ በዓልን ምክንያት በማድረግ የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ያስተላለፉት መልዕክት

ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለ2015 ዓ.ም የትንሳኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን እያልኩ በዓሉ የጤናና የደስታ እንዲሆን መልካም ምኞቴን እገልጻለሁ ።
ውድ የሀገራችን ኢትዮጵያ ህዝቦች!
በዓልን ወደጅ ዘመድ ተሰባስቦ ቤት ያፈራውን ማዕድ እየተቋደሱ በተድላና በደስታ ማሳለፍ የተለመደ የቆየ ኢትዮጵያዊ ልማድ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ኑሮው የተጫጫናቸው፣ ጊዜ ዘንበል ያለባቸውና በየጊዜው እየደረሱ ባሉ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ክስተቶች ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ፤ ለተለያዩ አካላዊ፣ ስነልቦናዊና አዕምሯዊ ጉዳቶች የተዳረጉ በአጠቃላይ ውስብስብና ተደራራቢ ለሆኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተጋለጡ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ዜጎች በመኖራቸው ልናስባቸው አለንላችሁ ልንላቸው ይገባል።
በተለያዩ ጊዜያት የእነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች ህይወት ለመታደግ ሁሉን አቀፍ ርብርብ ሲደረግ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን ከችግሩ ስፋት አኳያ አሁንም ብዙ መስራት ያስፈልጋል።
በዚህ ረገድ ከተረፋቸው ሳይሆን ካላቸው ቀንሰው በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖቻችን ድጋፍ ላደረጉና በእንዲህ ዓይነቱ ሰናይ ተግባር የተሰማሩት አካላትን ጥረት በጉልበታቸው፣ በገንዘባቸው፣ በቁሳቁስና በሃሳብ ጭምር ላገዙ፣ ለተባበሩ፣ ላበረታቱና ለደገፉ ልበ-ቀና ባለሃብቶች፣ ነዋሪዎች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም በጎ ፍቃደኛ አገልጋዮችን በሙሉ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፣ በተጠቃሚ ወገኖችና በራሴ ስም እጅግ አድርጌ ከልብ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ፡፡
የዘንድሮውን የትንሳዔ በዓል ስናከብርም የሀገር ባለውለታዎችን፣ አቅመ ደካሞችን፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎችን እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች በማሰብና አቅም የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ በዓሉን ተደስተው እንዲያሳልፉ ከጎናቸው በመቆምና የጀመርነውን ሁለንተናዊ ጥረት ይበልጥ አጠናክረን በመቀጠል ሊሆን ይገባል።
ስለሆነም መልካም እየሰራን ለሰራነው መልካም ስራ በረከት በማግኘት ሰው ሆኖ የተፈጠርንበት ዓላማ በመተግበር ፀጋን
እንድንቋደስ ባለሃብቶችን፣ ህብረተሰቡንና ተቋማትን በማስተባበር፣ ማዕድ በማጋራትና የተለያዩ ሰብዓዊ ተግባራትን በማከናወን ለወገኖቻችን ያለንን ፍቅር፣ ትህትናና አክብሮት በተግባር እንድናሳይና ሁላችንም ማህበራዊ ኃላፊነታችንን እንድንወጣ በዚህ አጋጣሚ ከአደራ ጭምር መልዕክቴን አስተላልፋለሁ።
መልካም በዓል!
Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *