በአረጋውያን የተሻለ ተጠቃሚነትና የትውልድ ቅብብሎሽን በተመለከተ የሚዲያና የባለድርሻ አካላትን ሚናና ተሳትፎ ለማሳደግ ያለመ የምክክርና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሄደ

(አዳማ፣ ሚያዚያ 12/ 2015 ዓ.ም)
የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለአረጋውያን የተሻለ ተጠቃሚነትና የትውልደ ቅብብሎሽነ በሚመለከት የሚዲያና የባለድርሻ አካላትን ሚናና ተሳትፎ ለማሳደግ ያለመ የምክክርና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በአዳማ አካሂዷል።
በመርሀ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፋት የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ አረጋውያን በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካው መስክ አሁን ለተደረሰበት ደረጃ ደማቅ አሻራ ያኖሩና ጠንካራ መሰረት የጣሉ ጥበብን ተጠቅመው ሀገር ያቀኑ ባለውለታዎች ቢሆኑም በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ክስተቶች እንዲሁም በማህበራዊ እሴቶች መሸርሸር ምክንያት ለከፋ ችግር እየተዳረጉ ይገኛል ብለዋል።
በመሆኑመ መንግስት የሀገር ባለውለታ የሆኑ የአረጋውያንን ችግር ለመፍታት፣ መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ፣ በልማቱ ተካታችና ተሳታፊ ለማድረግና ከትሩፋቱም ፍትሃዊ ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየሰሩ መሆናቸውንና ያላቸውን ፀጋና እሴት በትውልድ ቅብብሎሽ ማሻገር ተገቢ እንደሆነ ገልጸዋል።
ከመንግስት በተጨማሪ የተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እያበረከቱ በመሆኑ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስም አመስግነዋል። ከችግሩ ስፋት አኳያ ወደፊትም ጥረቱ ቀጣይነት እንዲኖረውም ሚኒስትር ዴኤታዋ በአጽዕኖት አሳስበዋል።
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን የሀገር ተረካቢና ባለቤት የሆነው ወጣቱ ትውልድ ጀግኖች አባቶች በከፈሉት መስዋዕትነት ጠብቀው ያቆዯትን ሉዓላዊት ሀገር ተረክበው ለቀጣዩ ትውልድ ልማትን፣ ሰላምን፣ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ብሎም ባህላዊና ማህበራዊ እሴቶችን ይበልጥ በማጎልበት ማስተላለፍ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ሆኖም በስነምግባርና በእውቀት የታነፀ፣ የተማላ ሰብዕና የተላበሰ፣ ሀገር ወዳድና ጠንካራ የስራ ባህል ያለው፣ አካላዊና አዕምሯዊ ጤንነቱ የተጠበቀ፣ በማንነቱ የሚኮራና ኃላፊነት የሚሰማው ወጣት ትውልድ በማፍራት ረገድ ከቤተሰብ ጀምሮ የሚዲያ አካላትና ሌሎችም የድርሻቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በአዋጅ የተሰጠውን ስልጣንና ኃላፊነት መሰረት በማድረግ የአረጋውያንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት እንዲያስችል የአረጋውያንና የቤተሰብ ጉዳዮችን የሚመለከት አዲስ አደረጃጀት በማቋቋም፣ በበጀትና በሰው ሀይል በማሟላት፣ የአሰራር ማዕቀፍ በማዘጋጀት ወደ ስራ መግባቱን የገለጹት የአረጋውያንና ቤተሰብ ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ ሮበሌ ናቸው።
እንደስራ አስፈጻሚው፤ የአረጋውያን ሆነ የቤተሰብ ጉዳይ በሁሉም ዘርፍ ውስጥ እንዲካተትና ተፈፃሚ እንዲሆን የተቋማት አካቶ ትግበራ፣ ቁጥጥር፣ ክትትልና ድጋፍ አሰራር መዘርጋቱንና ተጠያቂነትን ለማስፈን እየተሰራ መሆኑንም አያይዘው ተናግረዋል።
በመድረኩ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አቶ ደረጀ ታዬ በአረጋውያንና የሚዲያ ሚና ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ጽሁፍ አቅርበዋል።
አረጋውያንን አስመልክቶ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለውን የተዛባ አመለካከት ለመለወጥ፣ በመብቶቻቸው ዙሪያ ግንዛቤን ለማስረጽ እንዲሁም በድጋፍና ክብካቤ ተግባራት ላይ የባለድርሻ አካላትን ሚናና ተሳትፎ ለማሳደግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ጨምሮ በተለያዩ አካላት ሰፋፊ ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም ከተደራሽነታቸው አኳያ በተለይ መገናኛ ብዙኃን ሚናቸው እጅግ የላቀ በመሆኑ አረጋውያንን ማዕከል ያደረጉ ተግባራትን በማከናወን ሙያዊና ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አቶ ደረጀ ጥሪ አቅርበዋል።
ስለአረጋውያን አጠቃላይ ሁኔታ ያተኮረ ፅሁፍ ያቀረቡት የሄልኝፕ ኤጅ ኢንተርናሽናል ተወካይ አቶ አማኑ ዋቤ በበኩላቸው፤ ሁላችንም “ለአረጋውያን የሚራራ ልብ፣ የሚለግስ እጅ እና የማይዝል ጉልበት ሊኖረን ይገባል” ሲሉ ገልጸዋል።
በቀረቡ መነሻ ጽሁፎች ላይ ሰፊ ውይይት የተካሄደ ሲሆን ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በሚመለከታቸው አካላት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።
በመድረኩ ከተለያዩ የፌዴራልና የክልል ተቋማት፣ ከሚዲያ አካላት እና ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *