“የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ከሚንቀሳቀሱ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር በትብብር ይሰራል” – ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ

(አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 14/2015 ዓ.ም) ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ “የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ከሚንቀሳቀሱ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር በትብብር እንደሚሰራ የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለጹ።
ይህን የገለጹት ወገኔ ኢትዮጵያውያን ማህበር ሃያ ሶስተኛ አመት የምስረታ ክብረ በዓል እና የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር በሂልተን ሆቴል ባካሄደበት ወቅት ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ነው።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሀገራችን በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ክስተቶች ምክንያት በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን ለመደገፍ “አንድ ዲያስፖራ ለአንድ ህፃን” እንዲሁም “እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ጊዜያት ያካሄደውን ሰፋፊ የማህበረሰብ ንቅናቄ ተከትሎ “ለወገን ደራሽ ወገን ነው” በሚል ቀና አመለካከት ኑሮአቸውንና ስራቸውን በውጭ ሀገር ያደረጉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የምግብ፣ የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎች የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ድጋፎችን ሲያደረጉ መቆየታቸውን ሚኒስትሯ አስታውሰዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ ወገኔ የኢትዮጵያውያን ማህበር ትልቅ ማሳያ ነው ያሉት ሚኒስትሯ ላለፉት 23 ዓመታት በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ህጻናትን፣ ቤተሰቦቻቸውን እና በከፍተኛ የኑሮ ችግር ወስጥ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመደገፍ ላበረከተው የላቀ ሀገራዊ አስተዋጽኦ በተጠቃሚ ወገኖች ስም ከልብ አመስግነዋል።
ማህበሩን ጨምሮ ሌሎች በሀገራችን የሚገኙና በበጎ አድራጎት ስራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ወገኖቻችን የገጠሟቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት እያደረጉት ያለው ጥረት እንዲሳካ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ትብብርና እገዛ እንደማይለየያቸው ገልጸዋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ወደፊትም የችግሩን ስፋትና ጥልቀት በሰፊው ለህብረተሰቡ ከማስገንዘብ ጎን ለጎን ቅንጅታዊ አሰራሮችን በመዘርጋት እንዲሁም የማህበረሰቡን እውቀት፣ ሀብት፣ ጊዜና ጉልበት በማስተባበር ለወገኖቻችን የተሻለ ተጠቃሚነት በትጋት ይሰራልም ብለዋል።
የወገኔ ኢትዮጵያውያን ማህበር መስራችና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ህሌኒ ለገሰ በበኩላቸው የማህበሩን የ23 አመታት ጉዞ እና በቀጣይ ሊከናወኑ በታቀዱ ተግባራት ዙሪያ ሰፊ ገለፃ አድርገዋል።
የማህበሩ ጥረት ፍሬ እንዲያፈራና አገልግሎቱን የበለጠ ተደራሽ ማድረግ እንዲችል ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ወ/ሮ ህሌኒ ጥሪ አቅርበዋል።
Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *