የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በፀጋ በላቸው ጉዳይ ላይ የሰጠው የምስጋና መግለጫ

ሚኒስቴር መ/ቤቱ ድርጊቱ ከተከሰተበት ዕለት ጀምሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መረጃ በመለዋወጥ ተገቢው ፍትህ እንዲተገበር ክትትል ሲያደርግ ቆይቶ በፖሊስና በህዝብ ትብብር አሁን ተበዳይ በሰላም ወደ ቤተሰቧ የተመለሰች ቢሆንም የወንጀል ተጠርጣሪውና ተባባሪዎች ላይ የሚደረገው ክትትል ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን ለዚህ ውጤት ትብብር ላአደረጋችሁ ሁሉ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከፍ ያለ ምስጋናውን ያቀርባል።

የሐዋሳ ከተማ ነዋሪ እና የዳሸን ባንክ ባልደረባ የሆነችው ወ/ሪት ፀጋ በላቸው የተባለች ግለሰብ በቀን 15/9/2015 ዓ.ም ከስራ ወጥታ ወደ ግል ጉዳዯ በምታመራበት ወቅት በተለምዶ አሮጌው መነኻሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሐዋሳ ከንቲባ የግል ጠባቂ ጠልፋ እንደተፈጸመባት የክፍለ ከተማው ፓሊስ መምሪያ መግለጹ ይታወቃል።

ይህንንም ተከትሎ የሐዋሳ ከንቲባ ጽ/ቤት እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት የተፈጸመውን ድርጊት አውግዘው መግለጫ ማውጣታቸው ይታወሳል።

ጠለፋ ከግለሰብ ፈቃድ ውጭ በሀይል የሚፈጸም፣ እጅግ አስነዋሪ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ህገወጥ ድርጊት ከመሆኑም በላይ ዜጎች በአለምና ሀገር አቀፍ ደረጃ የተቀመጡ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን በእጅጉ የሚጻረሩ በመሆኑ የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በወ/ሪት ፀጋ በላቸው ላይ የደረሰባት የጠለፋ ወንጀል ድርጊት ተገቢውን የፍትሕ ውሳኔ አግኝቶ ለሌሎች ማስተማርያ እንደሚሆን በፅኑ ያምናል።

በመሆኑም የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ ተፈፀመ የተባለውን የወንጀል ድርጊት መሰረት በማድረግ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር ለማዋልና አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸወ አካላት ጋር ይሰራል።

በዚህ አጋጣሚ በሴቶች መብት ዙሪያ የሚሰሩ ተቋማትን ጨምሮ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው እየተንቀሳቀሱ ለሚገኙ የክልል ቢሮዎች እና የፍትህ አካላት በሙሉ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አድናቆቱን ይገልፃል።

በሌላ በኩል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቀጣይም ጉዳዩን በቅርበት በመከታተል መረጃውን ለህዝብ ይፋ የሚያደርግ መሆኑን እያስታወቀ፤ የተበዳይ ቤተሰብም እና ተበዳይ እንዲሁም ህብረተሰቡ ውጤቱን በትዕግስት እንዲጠባበቁ በአክብሮት ይጠይቃል።

Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *