ህጻናትን አስመልክቶ በድህረ ግጭት ተግባራት እና ቀጣይ ድጋፎች ዙሪያ ከተመድ ዋና ጸሀፊ ልዩ መልዕክተኛ ሚስ ቨርጂኒያ ጋምባ ውይይት ተካሄደ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ህጻናትን አስመልክቶ በድህረ ግጭት ተግባራት እና ቀጣይ ድጋፎች ዙሪያ ከተመድ ዋና ጸሀፊ ልዩ መልዕክተኛ ሚስ ቨርጂኒያ ጋምባ ጋር ውይይት አካሄዱ።

ውይይቱ በዋናነትም በአማራና በአፋር ክልሎች የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደሀገር በተለይ ግጭትን አስቀድሞ ከመከላከል፣ በህጻናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ከመከላከል እና የተፈናቀሉን መልሶ ከማቋቋም አኳያ በተከናወኑ ስራዎች ዘሪያ መረጃ ለመለዋወጥ እንዲሁም በቀጣይ ለሚከናወኑ ተግባራት ድጋፎችን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመወያየት ያለመ እንደሆነ ተገልጿል።

በዕለቱ የህፃናት መብትና ጥበቃ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጌታቸው አሊቶ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቅድመ እና ድህረ ጦርነት ወቅት ከህጻናት ጋር በተያያዘ ያከናወናቸውን ተግባራት ሪፖርት ለልኡክ ቡድኑ በዝርዝር አቅርበዋል።

በውይይቱ ወቅትም ከግጭቱ በኃላ የችግሩን ስፋት ለመገንዘብ የዳሰሳ ጥናት መካሄዱን፣ ምላሽ ሰጪ ኮሚቴ መቋቋሙን፣ የሚመለከታቸው አካላትን ያሳተፈ እቅድ መዘጋጀቱንና ወደ ተግባር መገባቱን በተቋሙ የበላይ አመራሮች ተጠቁሟል።

በትግበራ ሂደትም ጥቃት ለደረሰባቸው፣ ለተፈናቀሉና ለተለያዩ የአእምሮ ጤናና ለስነልቦና ጉዳት ለተጋለጡ ወገኖች የተቀናጀ ተግባራዊ ምላሽ ለመስጠት እንዲያስችል ከክልሎች፣ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢኒስትቲዩት እንዲሁም ከዩኒሴፍ እና ከአለም ባንክ ጋር በመቀናጀት በርካታ ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸው በሰፊው ተብራርቷል።

የሳይኮ ሶሻል ድጋፍ አገልግሎት ለሚሰጡ የሴክተር ባለሙያዎች እና ተጽዕኖ ፈጣሪ አካላት ስልጠና መሰጠቱን እንዲሁም የምግብ፣ የአልባሳት፣ የንጽህና መጠበቂያን ጨምሮ ለማዕከላት ግልጋሎት የሚውሉ ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጉም ተመልክቷል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በግጭት ወቅትም ሆነ ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ እንደሀገር ሴቶችና ህጻናትን ጨምሮ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ህይወት ለመታደግ እየተደረገ ላሉ ጥረቶች ዩኒሴፍ፣ ሌሎች የተባበሩት መንግስታት አጋር ድርጅቶች እንዲሁም የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ሲደገፉ መቆየታቸውን በውይይቱ ላይ ተነስቷል።

የልማት አጋራቱ ላበረከቱት ሰብዓዊ አስተዋጽኦም በኢትዮጵያ መንግስት፣ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና በተጠቃሚ ወገኖች ስም ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል። ዜጎችን በዘላቂነት መደገፍና ማቋቋም እንዲቻልም የተጀመረው ድጋፍ ቀጣይነት እንዲኖረው ጠይቀዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ ልዩ መልዕክተኛ ሚስ ቨርጂኒያ ጋምባ በበኩላቸው በግጭት ሳቢያ ለተጎዱ ህጻናት ጥበቃ በማድረግ ረገድ በመንግስት በኩል እየተሰሩ ያሉትን ስራዎችና የተገኘትን ውጤቶች አድንቀዋል።

ወደፊትም በህጻናት ላይ የመብት ጥሰቶች ከመፈጸማቸው በፊት አስቀድሞ ከመከላከል ባሻገር በተለያዩ ምክንያቶች ከቤተሰቦቻቸው የተለዩ ህጻናትን መልሶ ማቀላቀል ለሚያስችሉ ተግባራት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩልም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ግጭትን ከመከላከልና ሰላምን ከማስፈን ለሚከሰቱ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ክስተቶች ምላሽ ከመስጠት አኳያ እንዲሁም በቀጣይ እንደሀገር የሚከናወኑ ተግባራት ተገቢው ትኩረት እንዲያገኙ እና በጋራ መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ልዩ መልዕክተኛዋ ገልጸዋል።

Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *