በተጠናከረ የማኅበረሰብ ተሳትፎ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን በጋራ እንከላከል!! በሚል መሪ ቃል ሁለተኛው ህዝባዊ የንቅናቄ ኘሮግራም በድሬ ደዋ ከተማ አስተዳደር ተካሄደ፡፡

በተጠናከረ የማኅበረሰብ ተሳትፎ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን በጋራ እንከላከል!! በሚል መሪ ቃል ሁለተኛው ህዝባዊ የንቅናቄ ኘሮግራም በድሬ ደዋ ከተማ አስተዳደር ተካሄደ፡፡

መርሀ-ግብሩ በኢትዮጵያ ብሄራዊ መዝሙርና የሀገር ሽማግሌዎች ምርቃት የተጀመረ ሲሆን በእለቱ የሴቶችና መህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ የሚኒስቴር መ/ቤቱ የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሼቴ፣የምክር ቤት አባላት፣ የድሬ ደዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክቡር አቶ ከድር ጆሀር ፣ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች፣ የኃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት የንቅናቄ መርሀ-ግብሩ በተለያዩ ዝግጅቶች በደማቅ ስነስረዓት ተካሄደ፡:

በመርሃ ግብሩ ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደገለፁት ዜጎች በአገር ውስጥ ሰርተው መለወጥን ልምድ ማድረግ እንደሚገባቸው ጠቅሰው ነገር ግን ከሀገር ውጭ መስራት ከተፈለገ መስፈርቱን በማሟላት በስራና ክህሎት ሚኒስቴር በኩል በውጭ አገር ስራ ማሰማራት ተገቢ እንደሆነ ገልፀዋል። በመሆኑም በህገወጥ መንገድ በመጓዝ ዜጎች ለአደጋ እንዳይጋለጡ ቤተሰብ፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ብለዋል፡፡

ዜጎችን ከስደት በመመለስ ደረጃ የተደረገው ጥረት በጎ ስራ መሆኑን ገልፀው ቀጣዩ ሥራችን ስደትን የሚፀየፍ ትውልድ በመፍጠር ለዜጐቻችንም ሆነ ለአገራችን ክብርና ስራ ወዳድ የሆነ ወጣትን የማፍራት ስራ እንዲሰራ አሳስባለሁ ብለዋል።

በማከልም በሕገ-ወጥ ዝውውር ሳቢያ ክብርና ስብዕናው የሚዋረድበትና በባርነት ቀንበር ተጠምዶ የሚማቅቅበት መሆኑንን ገልጸዋል፡፡ የሰውልጅ በሕገ-ወጥ ዝውውር በየብስና በባህር የማለቁ መርዶ የውሎ ዜና እየሆነ ዓለምን ሲያዳርስና ልብ በሐዘን ሲሰበር ማየት የአዘቦት ገጠመኝ እየሆነ ቀጥሏል ብለዋል::

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት አየለች እሼቴ በኩላቸው የፌዴራል መንግስት አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን እና በሰው የመነገድና በህገ-ወጥ መንገድ ሰውን ድንበር ማሻገር ወንጀል ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጡ አዋጆች መሰረት ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከተሰጠው ኃላፊነት አንዱ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ከመፍጠር ባሻገር በሰዎች የመነገድና ሰዎችን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን የመከላከል፣ የወንጀሉ ሰለባ የሆኑ ተመላሽ ዜጎችን ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ ድጋፍ የመስጠት እንዲሁም ሀገራዊ የፍልሰት መረጃ የማደራጀት ስራዎችን ያከናውናል ያሉት ሚኒስትር ዳኤታዋ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላትን በማስተባባር መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከል እንዲቻል ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር በስፋት የሚታይባቸውን አካባቢዎች መሰረት ያደረገ ሀገራዊ የንቅናቄ መድረክ ማዘጋጀት አስፈላጊ ስለሆነ ይህ ሀገራዊ የንቅናቄ መድረክ ለሁለተኛ ጊዜ በዚህ በድሬ ደዋ ከተማ አስተዳደር ተካሄዷል ብለዋል፡፡

የድሬ ደዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክቡር አቶ ከድር ጆሀር የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር በማድረግ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመጨረሻም ከህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር ተያይዞ ፅሁፎች ከቀረቡ በኋላ ውይይት ተደርጎ የተለያዩ ግብአቶችና አስተያየቶች ተደርጉ ቀጣይ አቅጣጫ በመያዝ መድረኩ ተጠናቋል፡፡

Please follow and like us: