በአይነቱ ልዩ የሆነ የነጋዴ ሴቶች “መሰናክሎችን መስበር ድልድይ መገንባት” በሚል መሪ ቃል ኤክስፖ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ተከናወነ፡፡

(አዲስ አበባ ሰኔ 7/2015 ዓ.ም)
በሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ማሌሳ ኤቨንት አስተባባሪነት ከሰኔ 7-9 ቀን 2015 ዓ.ም ለሶስት ቀናት የሚቆይ የነጋዴ ሴቶች ኤክስፖ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር በዛሬው ዕለት ይፋ ተደርጓል፡፡

ኤክስፖው ሴቶች በስራ ፈጠራ፣ በአምራችነት፣ በንግድ፣ በገበያ ትስስር፣ በኢንዱስትሪ መሰረተ ልማት እና ተወዳዳሪነት ዙሪያ ያላቸውን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት የሚያሰፉበትን ዕድሎ እንደሚፈጥር የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትረ ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዪ ገልፀዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያግዙ ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችን፣ ፓኬጆችን እና ሌሎች የማስፈጸሚያ ስልቶችን በመቅረጽ ወደ ተግባር እንዲሸጋገሩ ያላሳለሰ ጥረት እያደረገ ይገኛልም ብለዋል፡፡

በንግድ ዘርፍ የሚገኙ ታዳጊ እና ወጣት ሴት ስራ ፈጣሪዎች ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች፣ አሰራሮችና ክህሎቶች ጋር ይበልጥ እንዲተዋወቁ፣ ጠቃሚ ልምድና ተሞክሮ እንዲቀስሙ እንዲህ ዓይነቱ አጋጣሚ ወሳኝ በመሆኑ ሴቶች እድሉን በሚገባ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ሚኒስትሯ በአፅእኖት ገልፀዋል፡፡

ሴቶች መብቶቻቸው ከተከበሩላቸው፣ ችግሮቻቸው ከተቀረፉላቸው፣ ጥረታቸውን ካበረታታናቸው፣ ላበረከቱት አስተዋጽዖ ተገቢው እውቅና ከተቸራቸው፣ ያላቸውን እምቅ አቅምና ተሰጥዖ፤ እውቀትና ክህሎት በመጠቀም ተጠቃሚ መሆን እንሚችሉም ጠቁመዋል፡፡በተጨማሪም ይህ አይነቱ ኤቨንት ቀጣይነት እንዲኖረው ሚኒስተሯ አሳስበዋል።

የማሌሳ ኤቨንት ዋና ስራ አስኪያጅና የኤቨንቱ አዘጋጅ ሰላማዊት ደጀን ለፕሮግራሙ መሳካት አስተዋፅኦ ላበረከቱ የመንግስትና የግል አጋር ደርጅቶች ምስጋና አቅርበዋል።

የፌዴራል ተቋማትና ሌሎች የልማት አጋር ድርጅቶች ትብብር የተዘጋጀው ኤክስፖው ምርት ከመሸጥና ማስተዋወቅ ጎን ለጎን የፓናል ውይይቶችና ከንግድ ስራ ጋር የተያያዙ ስልጠናዎች የሚሰጡበት ይሆናል፡፡

Please follow and like us: