የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም የቀጠናው ሀገራት በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ

የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም የቀጠናው ሀገራት በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ


(አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6፣ 2016 ዓ.ም) የሴት ልጅ ግርዛትን ለመከላከልና ለማስቆም በጀርመን ተራድኦ ድርጅት በሶስት ሀገራት ላይ እየተተገበረ ባለው የመጀመሪያ ዙር ፕሮጀክት አፈጻጸም ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ በቀጠናው የሚገኙ የሱዳን፣ ሶማሌ እና ሶማሌ ላንድ ተወካዮች ውይይትና የልምድ ልውውጥ አካሂደዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሙና አህመድ የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም የቀጠናው ሀገራት በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የሴት ልጅ ግርዛትን እና ያለዕድሜ ጋብቻን ጨምሮ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በሴቶችና ህጻናት ላይ ከሚያስከተለው አሉታዊ ተፅዕኖ ባሻገር በማህበረሰብ እና በሀገር ላይም ከፍተኛ ጫና እያሳደረ እንደሚገኝ የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታዋ መንግስት በ2025 ድርጊቱን ለማስቆም የገባውን ስምምነት ተፈጻሚ ለማድረግ የ5 ዓመት ብሔራዊ የድርጊት መርሀ ግብር በማዘጋጀት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የባህሪ እና የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት ሰፋፊ የግንዛቤ እና የንቅናቄ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነና በተለይ ድርጊቱ በስፋት በሚስተዋልባቸው አፋር እና ሱማሌ ክልሎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም የጀርመን ተራድኦ ድርጅት (GIZ) እና ሌሎችም አጋር አካላት ኢትዮጵያ የምታደርገውን ሁለንተናዊ ጥረት እየደገፉ መሆኑን ገልጸዋል።

ችግሩ አለም አቀፋዊ እና አህጉራዊ ገጽታን የተላበሰ እንደመሆኑ ድርጊቱን በማስቆም ረገድ የቀጠናው ሀገራትም ሆኑ በየሀገራቱ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና የአለም አቀፍ ተቋማት ትኩረት ሊሰጡ እና በትብብር ሊሰሩ ይገባልም ተብሏል።

የጀርመን ተራድኦ ድርጅት ፕሮግራም ኃላፊ ጃና ዌግማን በበኩላቸው የሴት ልጅ ግርዛትን ለመከላከልና ለማስቆም በመጀመሪያው ዙር የተደረገው ጥረት አበረታች እንደነበር ከሪፖርቱ መገንዘብ መቻሉን ተናግረዋል።

ችግሩን ለማስቆም እንዲረዳም የምዕራፍ ሁለት ፕሮጀክት ትግበራ እንደሚቀጥል እና ድርጅቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።

Please follow and like us: