“ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገባችሁ ሴት ተማሪዎችና ተመራቂዎች ራሳችሁን ከመለወጥ ባለፈ ሀገራችሁ ኢትዮጵያን የበለጸገችና ለሁሉም ዜጋ የምትመች እንድትሆን በትጋት የመስራት ኃላፊነት አለባችሁ”- ሚኒስትር ዲኤታ ወ/ሮ ሁርያ ዓሊ


(አዲስ አበባ፣ ህዳር 3 ቀን 2016 ዓ.ም)

ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ሴት ተማሪዎችና ተመራቂዎች ራሳችሁን ከመለወጥ ባለፈ ሀገራቸው ኢትዮጵያን የበለጸገችና ለሁሉም ዜጎች የምትመች እንድትሆን በትጋት የመስራት ኃላፊነት እንዳለባቸው የኢፌዲሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ወ/ሮ ሁርያ ዓሊ አሳሰቡ።

ሚኒስትር ዲኤታዋ ይህን ያሉት፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በ2015 የትምህርት ዘመን በከተማው በሚገኙ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ የመመረቂያ ውጤት ላስመዘገቡ እና ከከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ የዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት ላመጡ ሴት ተማሪዎች የማበረታቻ እውቅናና ሽልማት በሰጠበት ወቅት ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ነው፡፡

“ዘመናችን የውድድር ዘመን ነው፤ ውድድሩ ዓለም አቀፋዊም ጭምር ነው ያሉት ሚኒስትር ዲኤታዋ ዛሬ በውድድር ባስመዘገባችሁት የላቀ ውጤት እንደተሸለማችሁት ሁሉ ነገም በዓለም አቀፋ ደረጃ ብቁ ተወዳዳሪና አሸናፊ ሆናችሁ በመውጣት ራሳችሁን ከመለወጥ ባለፈ ሀገራችሁ ኢትዮጵያን የበለጸገች ብሎም ለሴቶች፣ ህፃናት፣ አካል ጉዳተኞችና አረጋዊያን ጨምሮ ለሁሉም ዜጋ የምትመች እንድትሆን በትጋት የመስራት ኃላፊነት አለባችሁ ሲሉ አሳስበዋል።

‘ዛሬ ሴት አትችልም’ ከሚለው የተሳሳተ አመለካከት ተላቃችሁ እና ‘ሴትነትን ለአልችልም’ ምክንያት ከሚያደርጉ መካከል አሸንፋችሁ ለዚህ መብቃታችሁ ወደፊት ለሚጠብቃችሁ ደረጃ መወጣጫ የሚሆናችሁን መሰላል አመቻችታቹኋል ብለዋል፡፡

በቀጣይም በጥልቀት መመራመርን፣ በቅንጅት መስራትን፣ የተግባቦት እና የስራ ፈጣሪነት ችሎታዎችን ማዳበር ይኖርባችኋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ወይንሸት ዘሪሁን በበኩላቸው ሴቶች በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ መስኮች የእኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እንዲችሉ ከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የቢሮው የሴቶች ዘርፍ ም/ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ መቅደስ ተስፋዬም በሀገራችን በተፈጠረው ለውጥ በርካታ ሴቶች በስራ ፈጣሪነት፣ በአመራር ሰጪነት እና ሌሎችም ሀገርን ከፍ በሚያደርጉ መስኮች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ጠቅሰዋል።

በስርዓተ-ፆታ እኩልነት የሚፈለገውን ለውጥ እንዲመጣ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ባለው የትምህርት ዘርፍም ሴቶች ውጤታማ መሆናቸው የሚያኮራና እንደ ሀገር ለተጀመረው የብልፅግና ጉዞ ተደማሪ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡

Please follow and like us: