የአገልግሎቶች ተደራሽነት – ለአካል ጉዳተኞች እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት

በዓለማየሁ ማሞ

ከ20ኛው ክፍለ ዘመን ጀምረው ከወጡና ልዩ ልዩ የአካል ጉዳት ያለባቸውን ሰዎች ምርታማና ብቁ ዜጎች ለማድረግ አስተዋጽዖ ካደረጉ ህጎችና ደንቦች መካከል እኤአ በ1973 ዓም የወጣው የተሐድሶ ህግ ነው፡፡ በዚህ ሰነድ ውስጥ ማንም አካል ጉዳት ያለበት ሰው በሁሉም ህብረተሰባዊ አገልግሎት የመሳተፍ መብት እንዳለው ሰፍሯል፡፡

ለአካል ጉዳተኞች መብቶች ከሚደረግ ጥበቃ ጋር በተያያዘም ከማንኛውም አገልግሎት ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ማድረግ ወንጀል መሆኑን ተደንግጓል፡፡ ይህ ድንጋጌ በተባበሩት መንግስታት አባል ሃገራት ዘንድ ስራ ላይ እንዲውል ተደርጓል።

እኤአ ከ1950 ዎቹ ጀምሮ ህጎች፣ ደንቦችና ፖሊሲዎች ወጥተው በጦር ሜዳ አካላዊ ጉዳት ለደረሰባቸው ጀግኖችና የተለያዩ አይነት አካል ጉዳት ላለባቸው ሰዎች ሃገር አቀፍ የምክር፣ የስራ ስምሪትና ህጋዊ የተሃድሶ አገልግሎት በመሰጠትና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ በማድረግ ምርታማ ዜጎች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል።

እኤአ በ1980 ዓም የአሜሪካ የአካል ጉዳተኞች መብት ጥበቃ ተቋም ማንኛውም ዜጋ አካል ጉዳተኛ በመሆኑ ማንኛውንም ህዝባዊ አገልግሎቶች እንዲያገኝና አቅሙ የፈቀደውን ስራ መስራት እንዲችል እንዲሁም ከመገለልና መድልዎ የጸዳ የአሰራር ስርዓት እንዲዘረጋና ህገወጥ ድርጊቶችን የሚፈጸሙ ተቋማትን መከላከል የሚያስችል ህግ አውጥቷል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በታህሳስ ወር 1993 ዓ.ም ባጸደቃቸው ሃያ ሁለት ደንቦችና ድንጋጌዎችን ስንመለከትም አካል ጉዳተኞች ምንም ልዩነት ሳይደረግባቸው በህብረተሰቡ ውስጥ ባሉ ሁሉም እድሎች እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግም በተለያዩ በህግ ማእቀፎች የአካል ጉዳተኞች ተደራሽነትን ማካተቱንና ለጉዳዩ አጽንኦት መስጠቱን እንመለከታለን፡፡

ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽነት ማለት ከአመለካከት ለውጥ ጀምሮ አካል ጉዳተኞች እኩል እድል እንዲያገኙና ፍላጎቶቻቸውንና እኩል ተጠቃሚነታቸውን በተለየ ሁኔታ በመመልከትና ትኩረት በመስጠት በተለያዩ ምርቶችና አገልግሎቶች አቅርቦቶች፣ በህንጻዎችና የመንገዶች ኮንስትራክሽን፣ በአካል ጉዳት አይነት ሊቀርቡ በሚገባቸው ልዩ ልዩ የቴክኔዎሎጂ ውጤቶችና በየተቋማቱ በሁሉም አቅም ሰዎች ሊጠቀሙባቸው የሚገቡ መገልገያዎችን በመገንባት በማሻሻል ምቹ የስራ አካባቢን መፍጠር ማለት ነው፡፡

የስራ አካባቢን ምቹ በማድረግ የአካል ጉዳተኞችን የመብት ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት አኳያ የሚያስፈልገው ራምፕ እና ሊፍት/ሊፍት ብቻ ነው የሚል የተዛባ አመለካከት ይስተዋላል፡፡ እነዚህን የቴክኔዎሎጂ ውጤቶች በሁሉም ተቋማት አሟልቶ መገኘት መልካም ጅምር ቢሆንም ከመሰናክል – ነጻ የሆነ ምቹ የስራ አካባቢ በማዘጋጀት በአገልጋይነት መንፈስ የተገልጋይ እርካታን መፍጠር ያስፈልጋል፡፡

  ከመሰናክል – ነጻ የሆነ ምቹ የስራ አካባቢ ማለትም ከበር እና ከመተላለፊያ ስፋቶች እስከ ወለል ፣ ከመብራት ቆጣሪ ቁመቶች እስከ በር እጀታዎች እንዲሁም እንደ አካል ጉዳቱ አይነት ልዩ ልዩ የድምጽና ሌሎች መረጃ ሰጪ ምልክቶች አሟልቶ መገኘት የተገልጋይንና አገልጋዮችን የስራ ግንኙነት ውጤታማ በማድረግ ረገድ የጎላ ድርሻ አለው፡፡ ለአንድ ትንሽ ልጅ፣ ለአንድ አረጋዊና ለአንድ ነፍሰ ጡር ሴት የምናደርገው ድጋፍ የተለያየ ቢሆንም ሁሉም ለአደጋ የተጋለጡ መሆናቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት ከእንቅፋት ነፃ የሆነ አካባቢ ሊፈጠርላቸው ይገባል፡፡

በቅርቡ የህንድ ደረጃዎች ቢሮ እና ከከተማ ልማት ሚኒስቴር ትብብር የተዘጋጀው ከእንቅፋት የፀዳ አካባቢ መመሪያ በሁሉም አዳዲስ የመንግስት ህንጻዎች እና የህዝብ መገልገያዎች፣ መንገዶች እና መጓጓዣዎች ውስጥ ከእንቅፋት ነፃ የሆኑ መገልገያዎችን እንዲያሟሉ የሚል ሀሳብ አስፍሯል። መመሪያው የመስማት ችሎታ ችግር ላለባቸው ሰዎችና ለተሽከርካሪ ወንበር ተጠቃሚዎች በቀላሉ ለመድረስ የሚያስችል መፍትሔ እንዲፈለግና ለእነዚህ የአካል ጉዳተኞች ጥቅም ሲባል የመስማት ችሎታ ምልክቶችን የመትከልና ሁለገብ የቢሮ መገልገያ ቁሳቁሶች እንዲያሟሉ ተገቢውን ዝግጅት እንዲደረግ ያዛል። በዚህ ሰነድ ውስጥ አዲስ በሚገነቡ ህንፃዎች ውስጥ መወጣጫዎች ፣ ለተሽከርካሪ ወንበር ተጠቃሚዎች የመጸዳጃ ቤት ማስተካከያ ፣ የብሬይል ምልክቶች እና የመስማት ችሎታ ምልክቶች በሊፍት ውስጥ እንዲዘጋጁ ያሳስባል።

የዊልቸር ተጠቃሚዎችን በቀላሉ መንቀሳቀስ እንዲችሉ በጠፍጣፋዎች ላይ የሚደረጉ የከርብ ቁራጮች እና ቁልቁለቶች ለዓይነ ስውራን ወይም ዝቅተኛ የማየት ችሎታ ላላቸው ሰዎች የእግረኞች ቅድሚያ የሚያሰጥ የመንገድ ማቋረጫ የነጭ ቀለም ምልክት (ዜብራ) በማዘጋጀት እንቅስቃሴቸው ቀለል ለማድረግ ጥረት እንዲደረግ ያመላክታል፡፡ ከእንቅፋት የፀዳ ዲዛይን አቅርቦት ስንል ከተደራሽነት አንጻር ከአጥር – ነጻና ውጫዊ እና ውስጣዊ የተገነቡ አካባቢዎች ፣ ዋና በሮች ፣ የመኪና ማቆሚያ ፣ የሕንፃ መግቢያ ፣ ኮሪደሮች እና አጠቃላይ የህዝብ መገናኛ ቦታዎች ላይ ያሉ መሰናክሎችን መለየትና ማስወገድን ያካትታል። አንድ ተቋም ለዊልቸር ተጠቃሚዎችም የአካባቢ ጥበቃ መሰናክሎችን መለየትና ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል ሲባል ደረጃዎችን ፣ ጠባብና ከባድ በሮችን ፣ ከፍ ያሉ ጠረጴዛዎችንና ጣራዎችን ማስተካከልና ምቹ ማድረግ ማለት ነው ።

የአካል ጉዳተኞችን ተደራሽነት ከሚመለከቱ ዓለም አቀፍ የሕግ ማዕቀፎች መካከል የሕፃናት መብቶች ኮንቬንሽን (አንቀጽ 23) ፣ የአፍሪካ የሰብአዊ መብቶች ቻርተርና የILO ስምምነት የኢንተር አሜሪካን ኮንቬንሽን ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የማዕቀፎቹ ዋና የትኩረት አቅጣጫ በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚደርስ ሁሉንም አይነት መገለልና አድልዎ ማስወገድ ነው።የዘንድሮውን አለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በማስመልከት የተባበሩት መንግስታት ለተደራሽነት ልዩ ትኩረት የሰጠ መሆኑን “እንቅፋቶችን መስበር – አካታች ማህበረሰብ እና ልማት ለሁሉም ” በሚል ካወጣው መሪ ሃሳብ መረዳት ይቻላል። ከእንቅፋት የጸዳን አካባቢን ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ ማድረግ ስንል ሁሉንም አይነት መሰናክሎች በማስወገድ የአካል ጉዳተኞችን መብት እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን በተጨባጭ ማረጋገጥ ነው፡፡

 
 
 
በአካል ጉዳተኝነት ጽንሰ – ሀሳቦች ዙሪያ የሚከናወኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች፣ የተወሰዱ ትርጉም አዘል እርምጃዎች የአመለካከት ለውጦችን ከማምጣት በተጓዳኝ የማህበረሰቡን መልካም እሴቶች በማጎልበት ማህበራዊ እና ባህላዊ ደንቦች ከማሻሻል አንጻር የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ትኩረት የሚጠይቁ ተግባራት ናቸው፡፡
በዚህ መሰረት የህግ አስተሳሰብ ዋና ዋና ገፅታዎች ከሆኑት መካከል አንዱ ህግን የማህበራዊ ለውጥ መሳሪያ አድርጎ መጠቀም በመሆኑ የአካል ጉዳተኞችን መብት ለማክበርም ሆነ ለማስከበር በዓለምአቀፍ፣ በአህጉርም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ የወጡ የህግ ማዕቀፎችን በውል በመገንዘብ ለተግባራዊነታቸው ሁላችንም በባለቤትነት ፣ በቅንጅትና በትጋት ልንንቀሳቀስ ይገባል፡፡
Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *