አገልግሎቶችን ለተጠቃሚዎች በእኩልነት ማድረስ – ወረርሺኙን መግታት !”

በዓለማየሁ ማሞ
የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የኤድስ ቀን ኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭትን ለመግታት ለሚከናወኑ ተግባራት ልዩ ትኩረት በመስጠት “አገልግሎቶችን ለተጠቃሚዎች በእኩልነት ማድረስ – ወረርሺኙን መግታት !” በሚል መሪ ቃል ኅዳር 22 ቀን 2014 ዓ.ም የተለያዩ መርሃ ግብሮች በማከናወን ታስቦ ውሏል።
የመሪ ቃሉ ዋና ዓላማ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች ኤችአይቪ/ኤድስ በደማቸው ለሚገኝባቸውና በቫይረሱ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች የሚሰጡ አገልግሎቶችን በእኩልነት በማድረስ ወረርሺኙን መግታት ይቻል ዘንድ ሁሉም ዜጎች በባለቤትነት ስሜትና እንዲንቀሳቀሱና በተቀናጀና ዘላቂነት ባለው መንገድ ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ለማድረግና በኤድስ ህይወታቸውን ያጡ ወገኖችን ለማስታወስ ነው።
በ2020 የዓለም ትኩረት አቅጣጫ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በጤና በህይወትና በኑሮ እያስከተለ ካለው ተጽዕኖ በተጨማሪ እኩልነትን ከማስፈን ሰብዓዊ መብቶችን ፣ ከጾታ እኩልነት ከማህበራዊ ጥበቃና ከኢኮኖሚ እድገት ጋር እንዴት ጠንካራ ግንኙነት እንዳለው በመረዳትና ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት ዓለም አቀፋዊ ትብብርና የጋራ ኃላፊነት በመውሰድ በሁሉም ዘርፍ ስርጭቱን ለመግታት በባለቤትነት መስራት እንዲቻል ለማስገንዘብ ነበር።
የዘንድሮው የዓለም ኤድስ ቀን 2021 መሪ ሃሳብ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የአገልግሎቶች እኩል ተደራሽነት ላይ ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባና አጽንኦት የስጠ መሆኑን ከዓለም ጤና ድርጅት እና አጋር ድርጅቶቹ የተለያዩ ድረገጾች ላይ የሰፈሩ መልዕክቶች መገንዘብ ይቻላል፡፡
የዓለም የጤና ድርጅት የ2020 መረጃ በዓለማችን ከ37 ሚሊየን ሰዎች በላይ በኤች አይ ቪ የተያዙ ሰዎች መኖራቸውን፣ ከኤችአይቪ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች 680 ሺህ ሰዎች መሞታቸውንና ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን ሰዎች አዲስ በቫይረሱ መያዛቸውን እንዲሁም ከኤችአይቪ ጋር ከሚኖሩ ጎልማሶች መካከል 73 ከመቶ የሚሆኑት የዕድሜ ልክ የፀረ ኤችአይቪ ሕክምና (ART) ማግኘታቸውን ያመላክታል ።
የሀገራችን የኤችአይቪ ስርጭት 0.93% ሲሆን በዚህም ስሌት 669 ሺህ በላይ የሚሆኑ ወገኖች ኤች አይ ቪ በደማቸው እንደሚገኝ ሀገራዊ የኤች አይ ቪ ስርጭት ግምት (HIV ESTIMATES AND PROJECTION SPECTRUM 2019) ያሳያል።
ከእነዚህም ውስጥ 413,547 (61.8%) ያህሉ ሴቶች ናቸው፡፡ ሆኖም የስርጭቱ ምጣኔ ከአንድን ክልል ከሌላ ክልል ፣ በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች እንዲሁም በከተማና በገጠር ያለውን ስናነጻጽር የሚለያይና አዳዲስ በኤችአይቪ የመያዝ ምጣኔ በሚፈለገው መጠን እየቀነሰ እንዳልሆነ መረዳት አያዳግትም።
እኤአ አቆጣጠር በ2019 በሀገራችን 14,843 ሰዎች በኤች አይቪ መያዛቸውን ከእነዚህም ውስጥ 67 ከመቶው አዲስ የሚያዙና እድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች መሆኑ አምራችና የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎች መሆናቸው ለጉዳዩ የተለየ ትኩረት እንደሚያስፈልገው ያሳያል።
ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 20% ከመቶው አዳዲስ የተያዙ ሰዎች እድሜያቸው ከ20 – 24 ዓመት የሚሆኑ ወጣቶች ና 19% የሚሆኑት ደግሞ ከ0 – 4 ዓመት ውስጥ የሚገኙ ህጻናት ናቸው።
በአሁኑ ወቅት የኮቪድ – 19 ወረርሽኝ የዓለምን ትኩረት በእጅጉ የወሰደበት ጊዜ ላይ የምንገኝ ሲሆን በማህበረሰቡ ላይ እያስከተለ ያለውን ሁለንተናዊ ጫና ለመቀልበስ የሚደረገው ጥረት የኤች አይቪ ወረርሽኝ ቁጥጥር እና ኤድስ የማህበረሰቡ የጤና ችግር ወደማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ የተቀመጠውን የግብ ስኬት ይወስነዋል።
የኤች አይቪ/ኤድስ ስርጭትን ለመግታት በተፈለገው ፍጥነት ውጤታማ ለማድረግ በሃገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ዙሪያ ካጋጠሙ ችግሮች መካከል የኮቪድ – 19 ወረርሽኝ ፣ መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶች ተደራሽ ያለመሆን፣ ኤች አይቪ ተጋላጭ የሆኑ ወገኖቻችን የሚደርሰው መገለልና የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልዩነቶች መስፋት ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ እነዚህ ችግሮች ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ያለውን ጫና ይበልጥ እንዲባባስ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
በመሆኑም ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች በጥልቀት በመገንዘብ አስቸኳይ ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ ስትራቴጂካዊ ስልቶች በመንደፍ በተግባር ለመለወጥ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የኤድስ ፕሮግራም ወቅታዊ መግለጫ እንደሚያሳየው ጥምር የሆነው የኤችአይቪና የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሊገታ የሚችለው መድልዎና መገለልን በመቀነስ፣ የሰው ልጆችን ማዕከል ያደረጉ ስልቶችን በመቀየስና ሰብዓዊ መብቶችንና የስርዓተ ጾታ ጉዳዮችን መሰረት ያደረጉ ሁለንተናዊ ምላሾች መስጠት ሲቻል መሆኑን ያስረዳል።
በሀገራችን ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የጸረ ኤች አይቪ /ኤድስ ህክምና እንዳይቋረጥ የተደረገውን ሃገራዊ ጥሪ ተከትሎ መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት መካከል ከፍተኛ ትብብር ከማድረጋቸው በተጓዳኝ የጤና ባለሙያዎች ከፍተኛ ርብርብ ሁልጊዜም ሲወሳ የሚኖር ነው።
በዚህ መሰረት እኤአ በ2030 ኤድስ የማህበረሰቡ የጤና ችግር የማይሆንበትን ደረጃ ላይ ለመድረስ በተያዘው እቅድ የመጨረሻዎቹ አስር አመታት ውስጥ እንደመገኘታችን መጠን ከዚህ በፊት ያስመዘገብናቸውን ውጤቶች በማጎልበትና ክፍተቶቻችንን በመለየት ለመሙላት በዘንድሮው መሪቃል ላይ በተቀመጠው መልዕክት አገልግሎቶችን በእኩልነት በማድረስ ወረርሺኙን መግታት ይቻል ዘንድ በተቀናጀና ዘላቂነት ባለው መንገድ ድጋፋቸውን በመስጠት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለስኬታማነቱ በባለቤትነትና በትጋት እንዲንቀሳቀስ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጥሪውን ያቀርባል።
Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *