የ2016 የገና በዓልን አስመልክቶ በኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ የተላለፈ የመልካም ምኞት መግለጫ

ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ለ2016 የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል እንኳን በሰላም አደረሳችሁ፤ እንኳን አደረሰን እላለሁ።

በዓሉ የሰላም፣ የደስታና የጤና እንዲሆን በራሴና በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ስም ልባዊ ምኞቴን ለመግለፅ እወዳለሁ።

ክብረ በዓል በመጣ ቁጥር በሁላችንም ዘንድ የሚፈጥረው ልዩና አስደሳች ስሜት መኖሩ የሚያጠያይቅ አይደለም።

በሩቅም በቅርብም ያሉ ወዳጅ ዘመድና ጎረቤታሞች ተሰባስበው ቤት ያፈራውን ማዕድ በጋራ እየተቋደሱ፣ ያለው ለሌለው እያካፈሉ እና ስጦታ እየተሰጣጡ በተድላና በደስታ በዓልን ማሳለፍ የእኛ የኢትዮጵያውያን የቆየ ልማድና ባህል ነው።

 

ይሁንና በሀገራችን በተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ክስተቶች ሳቢያ ህይወታቸው የተነጠቁ፤ ቤት ንብረታቸውን ባላሰቡትና ባልጠበቁት ሁኔታ ያጡ በዚህም የተነሳ በአሁኑ ወቅት ለከፋ ችግር የተጋለጡ በርካታ ወገኖች በመኖራቸው የስጦታ በዓል የሆነውን የገናን ቀን እንዴት ብናሳልፍ ይሻላል የሚለው ሁላችንንም ሊያሳስበን ይገባል።

ስለሆነም የገናን በዓል ስናከብር በየአካባቢያችን የሚገኙ አቅመ ደካሞችን፣ አነስተኛ ገቢ ያላቸውና የተቸገሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን እንድስታውስ፤ በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉም ካለን በማካፈል፣ የቻልነውን በማድረግና በመደገፍ ሁላችንም እንድንረባረብ ሀገራዊ ጥሪዬን አቀርባለሁ።

ሁሉም ነገር አስደሳች የሚሆነው ሰላም ሲሆን ነውና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በተለይም ደግሞ መላው የአገራችን ሴቶችና ወጣቶች ሰላምን ለማስፈንና ለተጀመረው የእድገት ጉዞ መፋጠን ከምንጊዜውም በበለጠ ዘብ እንዲቆሙና በትጋት እንዲሰሩ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ።

Please follow and like us: