“የወንጪ – ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት ትልቅ ዕድልን የፈጠረ እና ትምህርትም የተገኘበት ነው” – የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር

“የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት” አካል የሆነው የወንጪ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም መንደር ምርቃት ስነስርዓት ላይ የታደሙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ፕሮጀክቱ የአካባቢውን ማህበረሰብ ማዕከል ባደረገ መልኩ መልማቱ ትልቅ ዕድል የፈጠረና ትምህርትም የተገኘበት እንደሆነ ገለጹ።

ኢትዮጵያ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የተለያዩ ፕሮግራሞች ቀርጻ ለተግባራዊነቱ በትኩረት እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች ብለዋል።

ሁሉም የልማት ስራዎች ሰው ተኮር መሆን አለበት በሚል የኢትዮጵያ መንግስት የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የወንጪ ደንዲ የኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት የዚህ ማሳያ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፥ እንዲህ ዓይነቱ የልማት ስራና የማስፋፊያ ፕሮጀክት የአካባቢውን ማህበረሰብ ማዕከል ባደረገ መልኩ መልማቱ ትልቅ ዕድል የፈጠረና ትምህርትም የተገኘበት ነው ብለዋል።

 

ፕሮጀክቱ የአካባቢው ማህበረሰብ ከቀየው ሳይፈናቀል መቋቋም፣ የተሻለና ዘመናዊ ኑሮ መኖር እንዲሁም በኢኮኖሚ ረገድ በአስጎብኚነትና በሌሎች መስኮችም መሳተፍ የሚችልበትን ዕድል የፈጠረ ነው ብለዋል።

የፕሮጀክቱ እውን መሆን በተፈጥሮ ውብ የሆነው የወንጪ አካባቢ ተደብቆ የቆየው የቱሪስት መስህብ እንዲታወቅ ከማድረጉም በተጨማሪ በተሰሩ መሠረተ ልማቶች ማህበረሰቡ ከሌላው አካባቢ እንዲገናኝ እና ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆን ሰፊ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ የማህበረሰቡን ህይወት በሚያሻሻልና በሚለውጥ እንዲሁም ቀጣይነት ባለው መልኩ እየተተገበረ ያለ እንደመሆኑ ማህበረሰቡ የፕሮጀክቱ ጠባቂና ተንከባካቢ እንደሚሆንም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ ኢኮኖሚ በማመንጨት ለሀገር ብልጽግናም ሆነ ለማህበራዊ ኑሮ እድገት ወሳኝ በመሆኑ ይህን ዓላማ ማሳካት እንዲችል ማህበረሰቡም የበኩሉን አስተዋጽዖ ማበርከት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

Please follow and like us: