የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያና ሶማሌላንድ መካከል የተደረገው ስምምነት የሁለቱ ሀገራት ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ በመሆኑ ስምምነቱን እንደሚደግፍ አስታወቀ

የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያና ሶማሌላንድ መካከል የተደረገው ስምምነት የሁለቱ ሀገራት ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ በመሆኑ ስምምነቱን እንደሚደግፉት አስታወቀ።

ምክር ቤቱ ይህን ያስታወቀው ስምምነቱን አስመልክቶ በዛሬው ዕለት ለሚዲያ አካላት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

በመግለጫው፥ የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ወጣት ፉአድ ገና፥ ስምምነቱ ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቅ፤ ቀጠናዊ ትስስርን የሚያጠናክር፤ ለሀገራችን ኢኮኖሚ ትልቅ አስታዋጽኦ ያለው፤ በጋራ የማደግና የመጠቀምን መርህ የተከተለ ለዲፕሎማሲያችንም ትልቅ ስኬትና አቅም መሆኑ ገልጿል፡፡

የጎረቤታሞች ህዝቦችን የጋራ ጥቅም ብሎም ወንድማማችነትና እህትማማችነትን ያረጋገጠ ለሌሎች ሀገራት ትምህርትና ማሳያ ነው ብሏል።

የሰላም፣ የንግግርና የድርድር መንገድ የአሸናፊነትና የስልጡን መንገድ መሆኑን በመጥቀስ የተደረሰውን ስምምነት በጽኑ እንደሚደግፍ አስታውቋል።

በቀጣይም አፈጻጸሙ ስኬታማ እንዲሆን ምክር ቤቱ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንደሚወጣ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

በዕለቱ ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች ከፕሬዝዳንቱ በተጨማሪ የምክር ቤቱ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የኢጋድ የወጣቶች የሰላምና ጸጥታ ፎረም ተወካይ ወጣት የሱፍ መሀመድ እንዲሁም የምክር ቤቱ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ወጣት ይሁነኝ መሀመድ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

Please follow and like us: