“በሴቶች ላይ የሚፈጸም ማንኛውም ጥቃት የሴቶችን ክብር የሚነካ፤ አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጉዳት የሚፈጥር ነዉ”። የሴቶችና ህፃናት ዘርፍ ሚንስትር ድኤታ ወ/ሮ አለሚቱ ዑመድ

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ላይ ግንዛቤ ማስጨበጥ የሚያስችል የውይይት መድረክ በወራቤ ከተማ እየተካሔደ ነው፡፡

በመድረኩ በሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶችና ህፃናት ዘርፍ ሚንስትር ድኤታ ወ/ሮ አለሚቱ ዑመድ እንደገለፁት “በሴቶች ላይ የሚፈጸም ማንኛውም ጥቃት የሴቶችን ክብር የሚነካ፤ አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጉዳት የሚፈጥር እንዲሁም ሴቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ ሙሉ በሙሉ የመሳተፍ ዐቅማቸውን የሚገድብ መሆኑን አስረድተዋል።

ሚንስትር ድኤታዋ አክለውም ባለድርሻ አካላት እንደየድርሻቸው ማኅበረሰቡን በማስተማር፣ የወንጀል ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ ለተጎጂዎች አስፈላጊውን የጤና፣ የማኅበረ ሥነ-ልቦና እና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ እና በቅንጅት በመሥራት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በተለይ በሀዲያ ዞን የሴት ግርዛት የተፈፀመ በመሆኑ በተቀናጀ አግባብ ድርጊቱን ለማስቆም ለረጅም ጊዜ ሲደረግ የነበረው ጥረትና የተገኘው ውጤት ወደ ኃላ እየተመለሰ ያለበት ሁኔታ መፈጠሩን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በሪፓርቱ መገለፁን አስታውሰዋል::

ሚንስትር ድኤታዋ አክለውም በዚህ መድረክ የተሳተፉ የክልልና የዞን የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በየአካባቢው ካሉ የማህበረሰብ አደረጃጀቶች ጋር የሰመረ ቅንጅት በመፍጠር አንዲትም ሴትና አንድም ህጻን በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በተለይም ደግሞ በግርዛት ሳቢያ የህልውና ህልማቸው እንዳይሟሽሽ ህዝባዊ ንቅናቄ በመፍጠር የአመለካከት ለውጥ በተጨባጭ እንዲመጣ የተጀመረውን ጥረት እንዲያጠናክሩና የመሪነት ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም በሀገር አቀፍ ደረጃ እየሠራ ያለውን ሥራ እንዲሁም ይህን ጉዳይ በሚመለከት አፋጣኝ እርምጃዎችን እንደሚወስድ በተለይም ከዞን እስከ ወረዳ በተቋቋሙ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ መዋቅሮች ምላሽ እንደሚሰጥ መግለፁ ይታወቃል ።

በተጨማሪም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ድርጊቱን ለመከላከልና ለማስቆም ክልሉም ሆነ ዞኑ የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ጥረት እንደሚደግፍና ከጎኑ እንደማይለይ አረጋግጠዋል ።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃዲያ ዞን በሻሸጎ፣ ሶሮና ምዕራብ ሶሮ ወረዳዎች በሴቶች ላይ በሚፈጸም ግርዛት ዙሪያ ባከናወነው ምልከታ ተጎጂዎች ለሚያጋጥማቸው የጤና እክል እየተሰጠ ያለው ድጋፍና ክትትል አጥጋቢ አለመሆን ሴቶች ከዘመናዊ ሕክምና ይልቅ ወደ ጎጂ ልማዳዊ አማራጮች እንዲያዘነብሉ ምክንያት መሆናቸውንና በተመሳስይም በሻሸጎ ወረዳ በማኅበረሰቡ ዘንድ ‘ጨበላ’ በመባል የሚታወቅ የተደጋጋሚ ግርዛት ጎጂ ልማድ በአካባቢው በበጋ ወራት በሁሉም ዕድሜ ክልል በሚገኙ ሴቶች ላይ በስፋት እንደሚፈጸም ተገልጿል።

በዚህ ጎጂ ልማድ የሚያልፉ ሴቶች ከጤና እክል ጀምሮ እስከ ሞት የሚያደርስ ጉዳት የሚደርስባቸው መሆኑ በክትትሉ ከተለዩ ግኝቶቹ መካከል መሆናቸውን በኮሚሽኑ በወጣው ሪፖርት መግለፁ ይታወቃል።

ዘጋቢ ስለእናት እስከዳር

Please follow and like us: