በሰላምና ሀገረ መንግስት ግንባታ የወጣቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችል ንቅናቄ ተጀመረ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የሰላም ሚኒስቴር በጋራ በመሆን “አድዋን ለዘላቂ ሰላምና ጠንካራ ሀገረ-መንግስት ግንባታ” መሪ ቃል በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ወጣቶችን ያሳተፈ የንቅናቄ መርሀ ግብር ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁን የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሙና አህመድ ገለጹ፡፡

የንቅናቄ መርሀ ግብሩ የአድዋ ድልን መነሻ በማድረግ የኢትዮጵያ ወጣቶች ታሪካቸውን፣ ባህላቸውን እና እሴቶቻቸውን በመገንዘብ ለዘላቂ ሠላምና ለሀገረ-መንግስት ግንባታ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ለማስቻል ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አስርተ አመታት የተከተለችው የፖለቲካ ስርዓት እና ወጣቱ ያለፈበት የትምህርት ስርዓት ወጣቱን ከሃገራዊ እይታ ይልቅ አካባቢያዊ እይታ ውስጥ እንዲታጠር ያደረገ፣ ከአንድነት ይልቅ በልዩነት አመለካከት አስተሳሰቡ የተቃኘ፣ በትብብር እና በታታሪነት ውጤት ላይ ከመድረስ ይልቅ በመገፋፋት እና በአቋራጭ መክበር የተንሰራፋበት እንዲሁም ከምክንያታዊነት ይልቅ በስሜት የሚገፋበት ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል፡፡

እንደሀገር ከገጠመን ፈተና ለመሻገር ወጣቱን ተከታታይነት ባለው ስልጠና እና ውይይት በማሳተፍ አመለካከቱን ማቅናት እና ለሃገራዊ አንድነት፣ ለሰላም፣ ለወንድማማችነት እና ለጋራ እድገት ያለውን አቅም እንዲጠቀም እና ሚናውን እንዲያጎለብት ለማድረግ የንቅናቄ መርሀ ግብሩን ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡

ወጣቱ የአድዋ ድል የመደመር ውጤት እና የጋራ ድል መሆኑን በሚፈለገው ደረጃ በመገንዘብ ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን እና የአርበኝነት ስሜትን እንዲላበስ ብሎም ሰላምን ለማጽናትና ለተሳካ ሀገር መንግስት ግንባታ በጎ አስተዋጾውን እንዲያበረክት ለማስቻል ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ታችኛው አስተዳደር እርከን ድረስ የሚሳተፉበት የንቅናቄና የውይይት መድረክ ይካሄዳል ብለዋል።

በመድረኩ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና ማህበራዊ ልማት የባህል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራሮች ፤የክልል ምክትል ርእሳነ መስተደደር፣ የክልል ሰላም ጸጥታ ቢሮ ሃላፊዎች፣ የክልል የወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተወካዮች እንዲሁም ሀገር አቀፍ የወጣቶች እና የሴቶች አደረጃጀቶች በተገኙበት የንቅናቄ ማሰፈጸሚያ መርሃ ግብር እና የውይይት መነሻ ሰነድ ቀርቧል፡፡

Please follow and like us: