15ኛው አለም አቀፍ የምልክት ቋንቋ ጉባኤ በቀጣዩ አመት በኢትዮጵያ ይካሄዳል

15ኛው አለም አቀፍ የምልክት ቋንቋ ጉባኤ በ2017 ዓም በኢትዮጵያ እንደሚካሄድ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በቀጣዩ አመት ዓለም አቀፍ የምልክት ቋንቋ ጉባኤን ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ለማዘጋጀት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል። ጉባኤው ከጥር 6 እስከ 9 ቀን 2017 ዓ.ም የሚካሄድ መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል።

ስምምነቱን የተፈራረሙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ትብብሩ ጉባኤውን በተሳካ መልኩ ለማካሄድ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል። በዚሁ ወቅት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ የዓለም የምልክት ቋንቋ ጉባኤ በቀጣይ አመት ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

ይህንን ተከትሎ ሚኒስቴሩ ጉባኤውን ከብሔራዊ መስማት ከተሳናቸው ማህበርና ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለማካሄድ ዝግጅት መጀመሩን ገልጸዋል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው የኢትዮጵያን ስም ከፍ የሚያደርጉና የአገራትን ትስስር ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራትን ዩኒቨርሲቲው እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ረገድ ጉባኤው በኢትዮጵያ እንዲካሄድ የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል። የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በመተባበር ጉባኤው የተሳካ እንዲሆን የሚጠበቅባቸውን ፡ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። በጉባዔው ከተለያዩ የአለም አገራትና ተቋማት የተወጣጡ ከ600 በላይ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ዘጋቢ ስለእናት እስክንድር

 

Please follow and like us: