ወንድማማችነት – ለህብረ ብሔራዊ አንድነት!

በዓለማየሁ ማሞ
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል “ወንድማማችነት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ በሃገራችን ለ16ኛ ጊዜ በመከበር ላይ ይገኛል፡፡
የዘንድሮው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል አከባበር ልዩ የሚያደርገው የአገራችን ህልውናና የህዝቦቿን አንድነት ለማስጠበቅ ተገደን በገባንበት ጦርነት ውስጥ ሆነን ጦርነቱን በአሸናፊነት ለመወጣት በኢትዮጵያዊነታችን ላይ የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ በአሸናፊነት በድል በመገስገስ ላይ በምንገኝበት በዚህ ወቅት የምናከብረው መሆኑ ነው ።
ይህን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ስናከብር ወንድማማችነትና ሕብረብሔራዊ አንድነት ከምንጊዜውም በላይ ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ሁኔታ እንዲሁም ታላቋን ኢትዮጵያን በማፍረስ ትናንሽ መንደሮችን ለመፍጠር የተነሱትን የአሸባሪው ጁንታ ቡድን አባሎችን፣ የውስጥ ተላላኪ ባንዳዎችንና የውጭ ታሪካዊ ጠላቶቻችን እያፈራረስን የምንገኝበት ወቅት ነው፡፡
ይህ ወቅት “በዘመቻ ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ግንባር አምርተው ጥምር ጦሩን በመምራት በሁሉም ግንባር ድል እየተመዘገበና የጠላት ሀይል እየተበታተነ ያለበት ወቅት መሆኑ የወገን ጦር ድል በድል እየደራረበ ሲገሰግስ በአንፃሩ የጠላት ኃይል ደግሞ በየጦር ግንባሩ ሽንፈትን እየደረሰበትና እየተደመሰሰ የሚገኝበት በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡
የአሸባሪው ሕወሐት ጀሌዎች በጠንካራው የወገን ጦር አይቀጡ ቅጣት ተቀጥተው እየተበተኑና እየተደመሰሱ በመሆናቸው ኅብረተሰቡ ራሱን በማደራጀት አካባቢውን እንዲጠብቅ፣ ጀሌዎቹን እንዲማርክ፣ እምቢ ያሉትንም እንዲደመስስ፣ የዘረፈውን ንብረትና ትጥቅ እንዳይወጣ እንዲያስቀር ከመንግሥት በቀረበው ጥሪ መሰረት በሁሉም ግንባሮች አካባቢዎች የሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ ላይ ይገኛል፡፡
ጥሪውን ተከትሎ ከአሸባሪው ቡድን ወረራ ነጻ በወጡ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ በማቋቋምና በሁሉም ግንባሮች በመገኘትና ፈጣን ምላሽ በመስጠት የወደሙ የመሰረተ ልማት አውታሮችንና የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን መልሶ በመገንባትና በመጠገን ወደ ስራ ማስገባት በደጀንነት የተሰለፈው የህብረተሰብ ክፍል ሃላፊነትና ግዴታ መሆኑን በመገንዘብ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተጀመረው የቅንጅት ስራ አካል በመሆን ድጋፍ ሰጪ አካላትን በማስተባበርና ሃገር አቀፍ የቀውስ ጊዜ ማገገሚያ እቅድ በማዘጋጀት ከተለያዩ ድጋፍ ሰጪ አካላት የፋይናንስ ድጋፍና የተለያዩ ቁሳቁሶችን ድጋፍ የማሰባሰብና ተደራሽ የማድረግ ስራዎችን ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ አጠናክሮ ለማስቀጠል ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ሚኒስቴር መ/ቤቱ በቅርቡ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ ንግድና የማህበራት ዘርፍ ምክር ቤት፣ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና አጋር አካላት በመቀናጀት የተሰባሰበውን የፋይናንስ የመድሃኒት፣ የህክምና መገልገያ እቃዎች፣ የዕለት ደራሽ ምግቦችንና አልባሳትን በሃገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ማለትም በአፋር፣ በደሴ፣ በባህርዳር፣ በዘንዘልማና በደብረብርሃን ከተማ በመገኘት በአጠቃላይ ከመቶ አስራ ስድስት ሚሊየን ብር በላይ በገንዘብና ከመቶ ሚሊየን ብር በላይ የቁሳቁስ ድጋፎችን በአሸባሪው ህወሃትና ተላላኪዎቹ ወረራ ጉዳት ለደረሰባቸውና ለተፈናቀሉ ወገኖች ማድረሱ የሚታወስ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ከአባቶቻቸው የወረሱትን የአሸናፊነትና የድል አድራጊነት ወኔ ተላብሰው፣ በተፋለሙበት አውዶች ሁሉ ድልን ተቀዳጅተው አገራችንን የጥቁር ሕዝቦች፣ የነጻነት ምልክት መሆኗን ለዓለም እንዳስመሰከሩ ሁሉ የአሁኑ ትውልድም የአገርን ህልውናና የሕዝቦችን አንድነትን በማስከበር የራሱን አሻራ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ እየደረገ ያለው ትግልና ትጋት የሚደነቅ ነው፡፡
“በዘመቻ ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት” እየተገኘ ያለውን ድል መሰረት በማድረግ ወጣቶች በማያውቁት አካባቢና ራዕይ በሌለው ጦርነት ገብተው እንዳያልቁ እጃቸውን ለመከላከያ ሰራዊትና ለክልል የፀጥታ ኃይሎች እንዲሰጡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥሪ መተላለፉ ይታወሳል፡፡
በተጓዳኝም ራዕይና ግቡ በማይታወቅ ጦርነት በዕውር ድንብር ጁንታው ያሰለፋቸው የትግራይ ወጣቶች እንደ ቅጠል እየረገፉ መሆናቸውን ገልጸው ለትግራይ እናቶች ባስተላለፉት መልዕክት ልጆቻቸው ራዕይ በሌለው ጦርነት እንዳያልቁ “ልጆቻችን የት ደረሱ?” ብለው መጠየቅ እንዳለባቸው ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡
ጥሪውን ተከትሎም በሺዎች የሚቆጠሩ የሽብር ቡድኑ ለውጊያ ያሰለፋቸው ታጣቂዎች እጃቸውን ለወገን ኃይል እየሰጡ ነው።
እጃቸውን የሰጡት ምርኮኞቹም ባለማወቅና በመገደድ ወደ ውጊያ መሰለፋቸውንና አሸባሪ ቡድኑ በደረሰበት ሽንፈት እጅ ለመስጠት መገደዳቸውን እየገለጹ ናቸው፡፡
የመገናኛ ብዙሃን የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ማህበራዊ የትስስር ገጽ ዋቢ በማድረግ “ኢትዮጵያ ተስፋ መቁረጥን ራሱን ተስፋ አስቆርጣዋለች። የማያውቋት ተነሡባት – የሚያውቋት ተነሡላት። የማያውቋት ዘመቱባት – የሚያውቋት ዘመቱላት። ኢትዮጵያ ማለት ሲነኳት ማንም የማያውቀውን ኃይሏን የምታወጣ ሀገር ናት። እየሆነ ያለውም ይሄነው” የሚል መልዕክት ማስተላለፋቸውን ዘግበዋል፡፡
እውነት ነው – ይህ የድል ብስራት እንደ አባቶቻችን የአደዋ የድል ታሪክ ለእኛ ኩራት ሲሆን የዛሬ ትውልድ ስራ ደግሞ ለቀጣይ የወኔ መነሻና የታሪካችን አንድ አካል ሲሆን ዛሬም ኢትዮጵያዊነት ለአፍሪካም ሆነ በቅኝ አገዛዝ ስር ወድቀው ለነበሩ በርካታ አገሮችና ህዝቦች ስም ብቻ ሳይሆን የአሸናፊነት ምልክትና በዓለማችን የትኛውም ጫፍ ለሚገኙ የጥቁር ህዝቦች የድል ተምሳሌትነታችን በድጋሚ የምናሳይበት ነው፡፡
በቅርቡ የሙዚቃ ከያኒዎቹ እነ አብነት አጎናፍር “አለን እኛ ልጆችሽ – ለኢትዮጵያ ወታደር ነን” በሚል በህብረት ባወጡት ስለሃገር በተቀነቀነ ዜማቸው ስንኞች ላይ
ለእናት ሃገር ለእማማ – ለሰንደቅ አላማ
ይከፈላል ሁሉም ነገር – በአንቺ ከመጣማ
ታላቅ እንደነበርሽ – ታላቅ ሆነሽ ሳናይ
አንተኛም ልጆችሽ – ለባዕድ ሃገር ሸንጋይ
የናቁሽ ይናቁ – የጠሉሽ ይራቁ
ያከበረሽ ይክበር – ኢትዮጵያ የኛ ሃገር
ከሌለሽ የለንም – መጠሪያ ስማችን
አትፈርስም አትፈርሺም – አንድ ነው ድምጻችን…. እያለ ይቀጥላል
ሃገራችን ኢትዮጵያ የዓለማችን የጥቁር ህዝቦች ቤትና ኩራት ስትሆን አብሮነትን የምታስቀድም፣ ወንድማማችነትንና እኩልነትን የምታቀነቅን ፣ በታሪኳ ሽንፈትን የማትወድ ስትሆን አሁን የገጠማትን ፈተና በብቃት በመመከት ላይ የምንገኝ መሆኑን በመገንዘብ የጀመርነውን የህልውና ዘመቻ በድል አጠናቀን የብልጽግና ጉዟችን ለማፋጠን አካባቢያችንን በንቃት በመጠበቅ፣ የሃገር መከላከያ ሰራዊቱን በመደገፍና ወደ ግንባር በመዝመት እንዲሁም ሁሉም በተሰለፍንበት የሥራ መስክ በጊዜ የለንም ስሜት ስኬታማ ውጤት ለማስመዝገብ ሊንተጋ ይገባል፡፡
Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *