የህጻናት የበይነ መረብ አጠቃቀም ደህንነትን ለማረጋገጥ በጋራ እንስራ!

የህጻናት የበይነ መረብ አጠቃቀም ደህንነትን ለማረጋገጥ በጋራ እንስራ!

የማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም መልዕክት መላላክ፣ ከቤተሰብና ጓደኞች ጋር የማውራት፣ ቪዲዮዎችን የመመልከት ልምድ በታዳጊዎች ዘንድ የሚዘወተሩ እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በአለም ላይ እንደሚስተዋለው ሁሉ፥ በኢትዮጵያም ከሚገኙ አራት ታዳጊ ህጻናት አንዱ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችንና በይነ መረብን እንደሚጠቀም ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

ይሁንና ህጻናት ስለ አጠቃቀም ደህንነት ምን ያክል ግንዛቤና እውቀቱ አላቸው የሚለው አጠያያቂ ጉዳይ ነው፡፡ ውሱን ከሆኑት ውጪ ብዙዎቻችንም የቴክኖሎጂና የበይነ መረብ ተጠቃሚ ነን ለማለትም ይከብዳል፡፡ ልጆች በበይነ መረብ ላይ ያላቸውን አጠቃቀም በተመለከተም ወላጆች የሚያደርጉት ቁጥጥርና ድጋፍም ውስንነት እንዳለው የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

አብዛኞቹም ከአጠቃቀሙ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ችግሮች አሊም ስጋቶች እንዳሉባቸው ሲገልጹ በስፋት ይደመጣል፡፡

በተለይ አሁን አሁኑ የቴክኖሎጂ እድገት፣ የበይነ መረብ ተደራሽነት መስፋፋትና ዘመናዊ ስልኮች በፍጥነት መበራከት በታዳጊ ህጻናት በበይነ መረብ ላይ ያላቸው አጠቃቀም ያልተለመደ ባህሪና ስጋት እየፈጠረ ይገኛል፡፡

በሀገራችን ህጻናት ለተለያዩ ጥቃቶች ሊያጋልጥ በሚችል መልኩ በይነ መረብን እንደሚጠቀሙ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ በተለይ ግላዊ መረጃዎቻቸውን ማለትም ሙሉ ስማቸውን፣ ስልክ ቁጥርና አድራሻቸውን በበይነ መረብ ላይ ማካፈል በጣም አደገኛና ታዳጊዎችን በኢንተርኔት በታገዘ ጥቃት አድራሾች እጅ እንዲወድቁ ሰፊ እድል ይፈጥራል፡፡

በማህበራዊ ሚዲያ ብቻ ያወቁትን ሰው በአካል ለማግኘት የሚደረግ ሙከራም ለታዳጊዎች በጣም አሳሳቢና ለጉዳት የሚዳርግ ድርጊት ነው፡፡ የእራሳቸውን ተገቢነት የሌላቸው ይዘቶችን ወይም ፎቶዎችን በማህበራዊ ሚዲያ ብቻ ለሚያውቋቸው ሰዎች ማጋራት ደግሞ ታዳጊዎች ለአጭበርባሪዎችና ለሌሎች ጥቃቶች ሊያጋልጡ ይችላልና በይነ መረብን ያለምንም ጥንቃቄና ደህንነት ወይም ድጋፍ ከመጠቀም መቆጠብ ይኖርባቸዋል፡፡

በአጠቃቀሙ ዙሪያ የህጻናትን ክህሎት ማሳደግና ማስተማር እንዲሁም የቤተሰቦችንና ሌሎች ቅርበት ያላቸው አካላትን ግንዛቤ ከፍ ከማድረግ ጎን ለጎን የህጻናትን አጠቃቀም በተገቢው መልኩ ለመቆጣጠር የሚረዳ የአጠቃቀም ስርዓት መዘርጋት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

ከዚህ አንጻር የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና የፍትህ ሚኒስቴር ከዩኒሴፍ እና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት የህጻናትን የበይነ መረብ አጠቃቀም ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያስችሉና ህጻናትንና ቤተሰብን ትኩረት ያደረጉ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል፡፡

የህጻናት ጥበቃ ባለሙያዎችን፣ የፖሊስ አካላትን፣ የፍትህ ባለሙያዎችን ክህሎትና አቅም የማጎልበት፣ የፖሊሲና ህግ አሰራሮችን የማጠናከር እንዲሁም በበይነ መረብ ታግዘው የሚሰነዘሩ ማናቸውም የህጻናት ላይ ጥቃቶች ወንጀል ተደርገው በትኩረት እንዲሰራባቸው ጥረት እየተደረገም ይገኛል፡፡

አለም አቀፍ የበይነ መረብ አጠቃቀም ደህንነት ቀን ህጻናትን ጨምሮ የሁሉንም አካላት ግንዛቤ ለማሳደግ፣ ቅንጅትና ትብብር ስርዓቶችን ለመዘርጋትና አዎንታዊ የሆኑ ዘርፈ ብዙ ምላሾችን ለማጠናከር በአጠቃላይም፤ በይነ መረብ ለሁሉም ማህበረሰብ አካታች በሆነና ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ ለተጠቃሚዎች ተደራሽ እንዲሆን መልካም እድሎችን እና ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር በማሰብ በየአመቱ በያዝነው የካቲት ወር ላይ የሚከበር ይሆናል፡፡

ወላጆች አርአያ ሁኑ፡፡ የልጆችን አጠቃቀም ሁኔታም በየጊዜው ተከታተሉ፤ ቁጥጥርም አድርጉ፡፡ ህጻናትም ጥንቃቄ አይለያችሁ፤ ሌሎች ስለተጠቀሙ ብቻ አትጠቀሙ፤ የማታውቁትን ጠይቁ መልዕክታችን ነው፡፡

Please follow and like us: