አለም አቀፍ የሴት ልጅ ግርዛት ያለመታገስ ቀን በፓናል ውውይት ተከበረ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) ጋር በመተባበር የዘንድሮውን አለም አቀፍ የሴት ልጅ ግርዛት ያለመታገስ ቀንን “Investing in FGM Survivor – Led Movement to End Female Genital Mutulation” በሚል መሪ ቃል በፓናል ውይይት ተከብሯል፡፡

በፓናል ውይይቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚ/ር የሴቶች ጥበቃና ምላሽ ዴስክ ሀላፊ ወ/ሮ ህሊና ላቀው በሴቶች ላይ የሚፈፀመው ግርዛት የሴቶችን መብት የሚጥስና ሴቶችን ለውስብስብ የጤና ችግር የሚዳርግ በመሆኑ ድርጊቱን ለማስቆም ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ሁሉም አካላት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሴቶች መብት ስርፀት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሙሉዓለም ጌታ በበኩላቸው የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን እና ብሔራዊ ጥምረት መመስረቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ያለውን የሰው ሀብት፣ እውቀትና ገንዘብ በማቀናጀት እና ጥምረቱን እስከ ወረዳ ድረስ በማቋቋም ስራዎችን ወጥ በሆነ መልኩ የመምራት፣ የማስተባበር እና የመደገፍ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኃይማኖት አባቶችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ የጎሳ መሪዎችን፣ የሴት የልማት ህብረቶችን፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን፣ የማህበረሰብ ሬዲዮ ፕሮግራሞችን እና የማህበረሰብ አደረጃጀቶችን በመጠቀም ድርጊቱን ለመከላከልና ለማስቆም የሚያግዙ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየቱን ጠቁመዋል።

ሆኖም በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው ልማዳዊ አመለካከት እና አፈፃፀሙ መልኩን እየቀያየረ መምጣቱ ድርጊቱን ለማስቆም የሚደረገውን ጥረት ፈታኝና አስቸጋሪ አድርጎታል ብለዋል።

የድርጊቱን ውስብስብነት በመረዳት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የተጀመሩ ቅንጅታዊ ስራዎች ይበልጥ ሊጠናከሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በዕለቱ ግርዛትን በተመለከተ በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና አፋር ክልሎች በጌጅ ኢትዩጵያ ሀገራዊ ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ወርቅነህ ያደታ የተደረጉ ጥናታዊ ጹሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በመድረኩ ላይ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከፍትህ ሚኒስቴር፣ የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) እና የተባበሩት መንግስታት የስነ ህዝብ ድርጅት (UNFPA) እና ሌሎች የልማት ድርጅት ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

Please follow and like us: