“ጥራት ያለው ትምህርት ለመላ አፍሪካዊያን ተደራሽ ማድረግ ችግሮችን ለመፍታትና የመጪው ትውልድ ተስፋን ብሩህ ለማድረግ ያስችላል” – ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጊ ተስፋዬ

“ጥራት ያለው ትምህርት ለአፍሪካውያን” በሚል ሃሳብ ሲካሄድ የቆየው የፖንአፍሪካ ወጣቶች ህብረት ጉባኤ ተጠናቅቋል።

 

ለአፍሪካ ወጣቶች ዘመኑን የሚመጥን ጥራት ያለው ትምህርት ተደራሽ ማድረግ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊያን ለመፍታት እንደሚያስችል የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጊ ተስፋዬ ገለጹ።

በጉባኤው ማጠናቀቂያ መርሀ ግብር ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት ሚኒስትሯ ዶ/ር ኤርጎጊ ተስፋዬ እንደተናገሩት፤ በመላ አፍሪካ ጥራት ያለው፣ 21ኛውን ክፍለ ዘመን የሚመጥን የትምህርት ስርዓት ተደራሽ ማድረግም የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን መፍትት ያስችላል።

 

“ሴቶችን ማስተማር ማህብረሰብን ማስተማር ነው” ያሉት ሚኒስትሯ፤ የፆታ እኩልነትን ለማስፋፋትም ትምህርት ወሳኝ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ጥራት ያለው ትምህርት ለመላ አፍሪካዊያን ተደራሽ ማድረግ ችግሮችን ለመፍታት፣ ኢኮኖሚን ለማሳደግ፣ ፈጠራን ለማስፋፋት፣ ያለን ሀብት ለመጠቀም እንዲሁም የዛሬና የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልዶችን ራዕይ ብሩህ ለማድረግ ቁልፍ መሠረት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በአፍሪካ ሁለተናዊ እድገት ለማምጣት ትምህርት ላይ መስራትና ኢንቨስት ማድረግ ተገቢ መሆኑንም አጽዕኖት ሰጥተዋል።

ጉዳዩ ዘርፍ ዘለል እንደመሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከትምህርት ሚኒስቴርና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራልም ብለዋል።

የአፍሪካ ወጣቶች ህብረት ዋና ፀሀፊ አቶ አህመድ ቢኒንግ በበኩላቸው፤ በአፋሪካ ዘመኑን የሚመጥን፣ ጥራት ያለው፣ ዘላቂና ሁሉን አካታች የሆነ የትምህርት ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ጥራት ያለው ትምህርት በአህጉሪቷ ተደራሽ ማድረግ ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ለማስመዝገብ ትልቅ ሚና አለው ብለዋል።

ጥራት ያለው ትምህርት ተደራሽ ለማድረግ ወጣቶችና የሚመለከታቸው አካላት በጋራ እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።

የህብረቱ አመራሮችና አባላት የተሳተፉበት ጉባኤ ጥራት ያለው ትምህርት ለአፍሪካውያን ተደራሽ ማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በመምከር የአቋም መግለጫ አውጥቷል። መግለጫው ለሁሉም የአፍሪካ ሀገራት እንደሚደርስ ተጠቁሟል።

Please follow and like us: