የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶች ምክር ቤት በይፉ ተቋቋመ

“የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶች ምክር ቤት ለወጣቶች ድምጽ” በሚል መሪ ቃል በተካሄደ ልዩ መርሀ ግብር የምክር ቤቱ ምስረታ ይፉ ሆኗል።

በስነስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሙና አህመድ ወጣቶች በሀገር ልማት ውስጥ ያላቸውን ሚና በአግባቡ እንዲወጡና ያለማንም ጣልቃ ገብነት የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው እንዲወስኑ፤ ችግሮቻቸውንም በራሳቸው እንዲፈቱ ለማስቻል የወጣቶች ምክር ቤት መመስረት ፋይዳው የላቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

የምክር ቤቱ እውን መሆን በጎ ለውጥን ለማምጣት በወጣቶች ኃይል ላይ ያለን የማይናወጥ እምነት ተጨባጭ ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የአስተዳደሩ ወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ምክር ቤቱ አይተኬ ሚና እንደሚጫወትም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ሆኖም ዓላማውን እንዲያሳካ ሊደገፍ ይገባል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ የሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ወጣቶች ምክር ቤቶች ለወጣቶች ድምፅ!” ሆነው ማገልገል እንዲችሉ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቁርጠኝነት ይሰራል ብለዋል፡፡

 

የምክር ቤቱ አመራሮችም በላቀ ተነሳሽነትና ትጋት እንዲሁም በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶች ምክር ቤት መመስረቱ ብዝሃነታችንን ከግምት ያስገባ የምክንያታዊነትን መርህ ተከትሎ ለሰላም ሞጋች ጠያቂና ለሀገር እድገት የላቀ አስዋጽኦ ማበርከት የሚችል ፤ ከጠባቂነት መንፈስ ተላቅቆ ስራ የሚፈጥር ወጣት እንዲበራከት መደላደል የሚሆን አዲስ አደረጃጀት እውን ማድረጋችን ነገ ላይ የሚታይ ትልቅ ውጤት አምጪ ነው ሲሉ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ የተከበሩ ከዲር ጁሃር ገልጸዋል፡፡

 

በቀጣይም የአስተዳደሩ ድጋፍና ቅንጅታዊ አሰራር እንደሚጠናከር ገልጸዋል፡፡

የድሬዳዋ ወጣቶች እና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍራኦል ቡልቻ በኩላቸው አስተዳደሩ በሚካሄዱ የኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ወጣቱን ቀጥተኛ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

ወደፊትም ቁጥር እየጨመረ የሚመጣውን የወጣቱን ፍላጎትና ጥያቄ ታሳቢ በማድረግ ከምክር ቤቱና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ምላሽ ለመስጠት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

 

ባለፉት ዓመታት ወጣቶች በተለያዩ አደረጃጀቶች ውስጥ እንዲካተቱ ቢደረግም ከፍትሃዊ ተጠቃሚነት አንጻር በርካታ ውሱንነቶች ያሉበትና የልማት ኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውም በሚፈለገው ደረጃ የጎላ አልነበረም ሲል የገለጸው የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዘዳንት ወጣት አሚዶ የሱፍ ነው።

ወጣቶችን እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ ማድረግ የችሮታ ጉዳይ አይደለም ያሉት ፕሬዝዳንቱ ጉዳያቸው በሁሉም የልማት እቅዶችና ፕሮግራሞች ውስጥ በዘላቂነት እንዲካተትና ተፈጻሚ እንዲሆን በትኩረት ምክር ቤቱ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

Please follow and like us: