የዘንድሮውን አለም አቀፍ የሴቶች ቀን አከባበርንና እስካሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ የተሰሩ ስራዎችን አስመልክቶ ከኢፌዲሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

በቅድሚያ የኢፌዴሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የዘንድሮውን አለም አቀፍ የሴቶች ቀን(ማርች 8) በዓል አከባበር እና ንቅናቄ መርሀ ግብር አስመልክቶ ባዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ጥሪያችንን አክብራችሁ የተገኛችሁ የሚዲያ አካላትን በሙሉ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፣ በኢትዮጵያ ሴቶችና በራሴ ስም እንኳን ደህና መጣችሁ ለማለት እወዳለሁ፡፡

እንደሚታወቀው፤ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በ19ኛው ክ/ዘመን መጀመሪያዎቹ አካባቢ በአብዛኛዎቹ የአውሮፓ ሀገራት የተከሰተውን የኢንዱስትሪና የኢኮኖሚ አብዮት ተከትሎ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሴቶች የሰራተኛውን ጎራ ቢቀላቀሉም ተገቢውን ጥቅም ማግኘት ባለመቻላቸው የተነሳ በወቅቱ ይደርስባቸው የነበረውን የመብት ረገጣና ጭቆና በመቃወም የነጻነትና እኩልነት ጥያቄን አንግበው አደባባይ በመውጣት ለአመታት ባካሄዱት የትግል እንቅስቃሴ የተገኘ የድል ቀን ሆኖ መከበር እንደጀመረ ታሪክ ያስረዳናል፡፡

አለም አቀፉ ማህበረሰብ በሴቶች ላይ የሚታየውንና የሚፈፀመውን ማናቸውንም ጭቆናና በደል ለማስቆም የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎችን ከማውጣት አንስቶ ማርች 8 የሴቶች ቀን ሆኖ እንዲከበር እስከመወሰን የደረሰ እርምጃ በመወሰዱ እለቱ በየአመቱ እየታወሰ እና እየተከበረ ይገኛል፡፡ በዓሉ የፆታ እኩልነትን በማስፈን ሴቶች ከነበረባቸው ድርብርብ ተጽዕኖ እንዲላቀቁና በኢኮኖሚያዊ፣ በማህበራዊና እንዲሁም በፖለቲካዊ መስኮችም እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማስቻሉም በላይ ቀኑ ሴቶች በህብረተሰቡ ውሰጥ የሚገባቸውን እውቅናና ስፍራ እንዲገኙ ትልቅ መሰረት የጣለ ታላቅ አለም አቀፍ ኩነት ነው፡፡

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በየዓመቱ የካቲት 29 ወይም ማርች 8 የሚከበረው የሴቶችን ሁለንተናዊ የትግል እንቅስቃሴና ውጤት ለመዘከር፣ ሰፋፊ ንቅናቄዎችን በማካሄድ በሴቶች ዙሪያ ለማህበረሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር፣ ወቅታዊ መረጃዎችን ለመስጠት እንዲሁም ሴቶች ላይ የሚሰሩ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ያስመዘገቡትን ስኬቶች የበለጠ እንዲያጎለብቱ እና የሚያጋጠሙ ችግሮችን ደግሞ በጋራ ለመፍታት እንዲረባረቡ ለማስቻል ነው፡፡ የዘንድሮውን አለም አቀፍ የሴቶች ቀንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ113ኛ ጊዜ “invest in women accelerate progress” በሚል መሪ ቃል እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ48ኛ ጊዜ “ሴቶችን እናብቃ፤ልማትና ሰላምን እናረጋግጥ!” በሚል መሪ ቃል ይከበራል፡፡

በዓሉን በዚህ መሪ ቃል ማክበር ያስፈለገው በየዘርፉ የተያዙ ውጥኖች በሚፈለገው ደረጃና ፍጥነት እንዲሳኩ በማስቻል ረገድ የሴቶች ድርሻ የላቀ መሆኑን አጽንኦት ለመስጠት፣ ህብረተሰቡን ለማስገንዘብና ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥ ለማስቻል ነው፡፡

ይህንኑ ለማሳካት ያመች ዘንድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሁሉም ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት የዘንድሮውን ማርች 8 ከዚህ ቀደም ከነበረው አከባበር በተለየ መልኩ ሴቶችን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ልዩ ልዩ መርሃ-ግብሮች ለማክበር በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡
በዓሉ የሚከበርበት አግባብ፡- በሀገር አቀፍ ደረጃ በዓሉ ከየካቲት 1 እስከ መጋቢት 18 ከፌደራል ጀምሮ እስከ ታችኛው የወረዳ መዋቅር ድረስ በቅንጅትና በትብብር የሚከበር ሲሆን ከሚሰሩ ዋና ዋና ተግባራት መካከልም ፡-
በድህረ- ጦርነትና በሰው ሰራሽ ምክንያቶች ጥቃት ለደረሰባቸውና ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችና ህፃናት ለመደገፍ 500 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሀብት በማሰባሰብ ድጋፍ ማድረግ፣
5000 ለሚሆኑ ለጥቃት ለተጋለጡ ሴቶችና ታዳጊ ሴቶች የቢዝነስ ክህሎት ስልጠና በመስጠት ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ እና ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ
ፆታዊ ጥቃት ለደረሰባችው ሴቶች አገልግሎት የሚሰጡ የተቀናጀ የአንድ ማዕከል እና የተሃድሶ ማዕከላት ማቋቋምና ማጠናከር፣
10,000አዳዲስ የሴት የልማት ህብረቶች ማቋቋምና ማጠናከር
10,000በህብረት ስራ ማህበራት የተደራጁ ሴቶችን ማጠናከር፣
250,000 ሴቶች የብድር ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች እንዲሰማሩ ማስቻል፣
500,000 ሴቶች በተመረጡ ጊዜና ጉልበት ቆጣቢ በሆኑ አዳዲስ ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙ ለማድረግ ግንዛቤ መፍጠር፣
8,000,000 ሴቶች በሌማት ቱርፋት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ፣
15,000 ሴቶች በተለያዩ የስራ እድል መስኮች ላይ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ፣
የሴቶችን ማህበራዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ለ2 ሚሊየን ሴቶች በጤናማ እናትነት፣ ሴቶች በጤና ተቋማት እንዲወልዱ፣ የማህጸን በርና የጡት ካንሰርን በሚመለከት ለሴቶች ግንዛቤ መፍጠር፣
በሀገሪቱ በተፈጠሩ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት ትምህርታውን ያቋረጡ ተማሪዎችን በመለየት ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ግንዛቤ መፍጠር፣፣
ሴቶች በሰላም ግንባታና ግጭት አፈታት ዙሪያ ጉልህ ሚና እንዲጫወቱ ለማድረግ በአጎራባች ክልሎች መካከል እንዲሁም በክልሎች ውስጥ ለሚገኙ 500 ሺህ ሴቶች የእርስ በእርስ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲያደርጉ ማመቻቸት፣
15 ሚሊየን ሴቶች “ቡና ለሰላም”በሚል መርህ በአካባቢያቸው ለሰላም ግንባታ ጉልህ ሚና እንዲጫወቱ ማድረግ፣
10 ሚሊየን ሴቶች በየደረጃው በሀገራዊ ምክክርና በሽግግር ፍትህ እንዲሳተፉ ማድረግ
10 ሚሊየን ሴቶችን በበጋ ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሳተፉ ማድረግ፣

በፌደራል እና በክልል ደረጃ ምን ተሰራ?
እቅዱ ለክልሎች የወረዳ ሲሆን፣ በየሳምንቱ በሚደረገው zoom meeting ክልሎች እየሰሩ ያለውን ስራ በመከታተል እየተገመገመ ይገኛል፡፡

ክልሎችም እቅዱን እንደ ክልላቸው ነባራዊ ሁኔታ በማገናዘብ አቅደው እስከ ዞኖችና ወረዳዎች ድረስ ለማውረድም ኦረንቴሽን በመስጠት የጀመሩ ሲሆን አሁን ላይ ወደ ተግባር በመግባት
ለችግር ለተጋለጡ ሴቶች የተለያዩ ምግብ ነክ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች በጥቅሉ እስካሁን በ1,402,535ብር በላይ መሰብሰብ ከ1000 በላይ ለሆኑ ሴቶች ድጋፍ ማድረስ ተችሏል
ለጤናማ እናትነት፣ የማህጸንና የጡት ካንሰርን በሚመለከት ለ728,984 ሴቶች የንቅናቄና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በመሰራታቸው እስካሁን 5000 የሚሆኑ ሴቶች የማህፀን ጫፍ እና የጡት ካንሰር ምርመራ በጤና ተቋማት አድርገዋል
15,365 ሴቶች በቁጠባና ብድር ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ሴቶች 65,000 ብር በመቆጠብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል፡፡
እስካሁን የተካሄዱ የንቅናቄ መድረኮችን በመጠቀም 225 በዩኒት ደም ማሰባሰብ ተችሏል፡፡
ከ1,593,148 ሴቶች በቡና ጠጡ እና የባህል ልዉዉጥ ተሳትፎ ያደረጉ ሲሆን ንቅናቄዉ ወደ ሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ሲደረግ የተያዘዉን ግብ ማሳካት እንደሚቻል ፍንጭ ሰጪ አፈጻጸም ታይቷል፡፡
653,346 ሰዎች በገጠር ክላስተር እና በከተማ ቀበሌዎች በሰላም ግንባታና ግጭት አፈታት ዙሪያ የሰላም ኮንፍረንስ ላይ በመታደም የግንዛቤ ማስጨበጫ አግኝተዋል፡፡
ከ200,870ሺህ ለሚበልጡ ሴቶች ጊዜያቸዉንና ጉልበታቸዉን በሚቁጥቡ ተስማሚ ቴክኖሎጂዎች ዙሪያ ግንዛቤ አግኝተዋል፡፡
2230 ሴቶች በተለያዩ የስራ እድል መስኮች ላይ ተሳታፊና ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
በተለያዩ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ላይ የተሳተፉ 2,261,324 ሴቶች በ676,595 ሄክታር የእርከን ልማት ስራ ላይ የተሳተፉ ሲሆን
429, 596 ሴቶችም በሌማት ቱርፋት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
1,230 ሴቶች በተለያዩ የስራ እድል ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
ከ1700 በላይ ሴቶች በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስኮች እየተሳተፉ ይገኛሉ
ልዩ ልዩ የእግር ጉዞዎች ፣ የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብና ውሀ የማጠጣት ስራዎችም ተጠናክረው እንደቀጠሉ ነው፡፡

ስለሆነም ለዕቅዱ ተፈፃሚነት አሁንም በየደረጃው የሚገኙ ሁሉም የመንግስት እና የሴት አደረጃጀት መዋቅሮች ሰፊ ርብርብ እንዲያደርጉ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና በራሴ ስም ጥሪ አቀርባለሁ፡፡
“ሴቶችን እናብቃ፤ ልማትና ሰላምን እናረጋግጥ!”

Please follow and like us: