የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከቻይናው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በጋራ ለመስራት የሚያስችል የሶስትዮሽ የስምምነት ሰነድ ሊፈራረሙ ነው።

ስምምነቱ በተለይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በቻይና ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ጋር በመተባበር ከቻይና መንግስት ጋር የተካሄደው ግኑኝነትና ማህበራዊ እድገትን ከማፋጠን አኳያ በትብብር ለመስራት የተደረገው ጥረት ፍሬ እያፈራ መምጣቱን ማሳያ መሆኑን ሚኒስትሯ ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገልጸዋል።

ስምምነቱ የሴቶችንና የአካል ጉዳተኞችን ህይወት ለማሻሻል የሚረዳ በአይነቱ በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነ ላቦራቶሪ በአዲስ አበባ ለመገንባት ያለመ እንደሆነ አስታውቀዋል። ቤተሙከራው በተለይ በአእምሮ ጤናና አካል ጉዳተኝነትን በተመለከተ የተለያዩ የምርምር ስራዎችን ለመስራት ያስችላል ሲሉ ተናግረዋል። ላቦራቶሪው በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ማእቀፍ እቅድ አካል መሆኑን ጠቁመዋል። በአይነቱ የመጀመርያ የሆነውን የላቦራቶሪ የግንባታ ሂደት ለማስጀመር መከናወን ስለሚገባቸው ስራዎች እና የሶስትዮሽ ስምምነቱ ምን መምሰል እንዳለበት የሁለቱም ሚኒስቴር መ/ቤቶች የሚመለከታቸው አመራሮች በተገኙበት ውይይት ተደርጓል::

በውይይታቸውም፥ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንዲሁም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር በለጠ ሞላ እቅዱን ለማሳካት በቅንጅትና በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል፡፡ ሁለቱም ሚኒስቴር መ/ቤቶች ለሴቶች፣ ህጻናት፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞችና አረጋዊያን ህይወት መሻሻል የሚረዱ ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ ለማድረግ አካታችነትን ባረጋገጠና ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በተቀመጠው መርህ መሠረት  እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል፡፡

Please follow and like us: