የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር የዘንድሮውን አለም አቀፍ የሴቶች ቀን – ማርች 8ን በማስመልከት ያስተላለፉት መልዕክት

ክቡራት ክቡራን
በቅድሚያ አለም አቀፍ የሴቶች ቀን – ማርች 8 ሴት እናቶቻችን እህቶቻችን ለመብታቸው የታገሉበትና ነፃነታቸውን ያስከበሩበትን የትግል ውጤተቻውን የምንዘክርበት ልዩ ቀን በመሆኑ የበዓሉ ባለቤት ለሆናችሁ ለመላው የሀገራችን ሴቶች እንኳን አደረሳችሁ፤ አደረሰን ለማለት እወዳለሁ።

በዚህ አጋጣሚ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ክብርት ሣህለወርቅ ዘውዴ ከውጭ ጉዞ ለሊት ገብተው እረፍት ሳያደርጉ በመሀከላችን በክብር እንግድነት በመገኘታቸው እጅግ አድርገን ለማመስገን እንፈልጋለን።

ይህን ልዩ የታሪካችን አሻራና እናት አባቶቻችንን በምንዘክርበትና በምናወሳበት ታሪካዊ ስፍራ በጀግንነት ለተዋደቁ እናቶቻችን ክብር ሲባል በነፃ በአዳራሹ እንድናከብር ለፈቀዱልን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለይ ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤን ከልብ እናመሰግናለን፡፡

የዘንድሮው አቀፍ የሴቶች ቀን – ማርች 8 በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ113ኛ ጊዜ ”invest in women accelerate progress” በሚል መሪ ቃል በሀገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ ለ48ኛ ጊዜ ”ሴቶችን እናብቃ፣ ልማትና ሰላምን እናረጋግጥ” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ የሚገኝ ሲሆን በዓሉ የሴቶችን ከወንዶች እኩል የመስራት፣ የመናገር፣ የመሰብሰብ እና ሌሎችም መብቶችን ለማስከበር ብዙ ጭቆናና ጫና ያንገሸገሻቸው ጥቂት ቆራጥ ሴቶች እ.አ.አ በ1990 ዎቹ የጀመሩት እጅግ መሪርና እልህ አስጨራሽ የትግል ውጤት ነው።

በሀገራችን 52% የሚሆነውን የህዝብ ቁጥር የሚወክሉት ሴቶች እንዲሆኑ ይታወቃል፡፡ ከቁጥር ባለፈ ትልቅ አቅም ያላቸውን የሴቶችን በልማት ማሳተፍ የሃገራችን የወደፊት እጣፈንታ ብሩህ እንዲሆን ይጠቅማናል፡፡ የማህበረሰባችን ሠላም፣ ልማትና ዕድገት እንዲፋጠንም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው እሙን ነው።

ሴቶች የማህበረሰባችን የጀርባ አጥንትና የሃገር ዋልታ መሆናቸውን የኢትዮጵያ መንግስት በሚገባ በማጤን ባለፉት 5 አመታት ከተደረጉ ወሳኝ የለውጥ ሥራዎች አንዱና ዋነኛው ሴቶች የሚገባቸውን ቦታ በመንግስት ከፍተኛ የስልጣን ኃላፊነት ቦታ እንዲመጡ እንዲሁም በሁሉም መስክ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያበረታታ እርምጃ መወሰዱ በጉልህ ይጠቀሳል።

በዚያን ወቅት በትግሉ ውስጥ የነበሩና የመሩ ቆራጥ ሴቶች ጀምረው የትግል ችቦውን አቀጣጥለው በአሁኑ ዘመን የምንገኝ ሴቶች በአደባባይ ቆመን ሀሳባችንን እንድንገልፅ ብቻም ሳይሆን እድሉ ከተሰጠን በየትኛውም የሀገራችን የእድገት እና የለውጥ ዘርፎች በውጤትና በመልካም ስነ-ምግባር የታጀበ ተግባር መፈፀም እንደምንች አቅማችንን ለአለም እንድናሳይ ፋና ወጊ ሆነውልናልና ለቀደምት እናቶቻችን ትልቅ ክብር ልንሰጥ ይገባል።

በየአመቱ ማርች 8 ሲደርስ በዓሉን የምናከብር እና ያገኘነውን ድል ብቻ የምንዘክርበት ሳይሆን በተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንዲሁም ፆታዊ ጥቃት ተጎጂ የሆኑ እናቶቻችን እህቶቻችንን የምንረዳበትና የምናስብበት ልዩ ቀን በመሆኑ ወጤትን ሊያመጡ በሚችሉ ዋና ዋና የሀገራችን ሴቶች ጉዳይ ላይ በማተኮርና ሀገራዊ የማስፈጸሚያ ዕቅድ በማውጣት ከክልሎች ጋር እቅዱን የጋራ በማድረግ ላለፉት 2 ወራት ሳምንታዊ የግንኙነት ስልት በመንደፍ ከክልሎች ጋር በቅንጅት የሚተገበሩበትና በየደረጃው በሚካሄዱ የንቅናቄ ስራዎች የተከናወኑ ተግባራት የሚገመገሙበት የሚመለከታቸውን አካላትን በማሳተፍ ሰፊ ስራ መስራት የተቻለበት በመሆኑ የዘንድሮ የበዓሉን አከባበርና የእቅድ ትግበራ ከወትሮ የተሻለ እንዲሆን እገዛ አድርጓል፡፡

በእስካሁኑ እንቅስቃሴም በክልሎች በዞኖች፣ በወረዳዎችና በከተማ አስተዳደሮች በየክፍለ ከተማው ለአቅመ ደካማ ሴቶችና ህፃናት እንዲሁም በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ለኢኮኖሚ ችግር ለተጋለጡ ወገኖቻችን በድምሩ 23,932 ዜጎች የምግብና የአልባሳት ድጋፍ መስጠት ተችሏል፡፡ ይህም በገንዘብ ሲተመን 99,263,932 ብር በላይ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል፡፡

በተጨማሪም በህብረት ስራ ማህበራት የተደራጁ ሴቶችን በማጠናከር በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማመቻቸት ሥራን መስራት ተችሏል፡፡ በዚሁ መሠረት ለቁጠባና ብድር በተሰራው የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ በየደረጃው የነበረውን የቅንጅት ችግር በመፍታት 1,799,412 በቁጠባ የተሳተፋ ሲሆን በዚህም 685,177,860.00 መቆጠብ ችለዋል፡፡

ሴቶችን በሌማት ቱሩፋት በተለይም ደግሞ በስጋና በእንቁላል ጣይ ዶሮ ፓኬጅ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል በተካሄደው የንቅናቄው ስራ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት እስካሁን ድረስ 604,943 ሴቶች በግልና በጋራ ከ5-10 ዶሮዎችን በማሰራጨት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ተችሏል፡፡

ከጤና ሴክተር ጋር በመቀናጀት በየደረጃው በተሰራው ሥራ የማህፀን ጫፍና የጡት ካንሰር ግንዛቤ ሥራ በሴቶች ልማት ኀብረት አማካይነት በጤና ባለሙያዎች የግንዛቤ ስራ በመስራት ከነዚህ ውስጥ የማህፀን በር ካንሠር ምርመራ የደረጉ ሴቶች 31,279 ሲሆኑ የማህፀን ጫፍና የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ በጤና ባለሙያዎች በማድረግ ችግሩ የታየባቸው የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል።

የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ ሂደትን ለማጠናከር ያሉ ጥንካሬና ድክመቶችን በመለየት የተለያዩ ድጋፎችን ማድረግ ተችሏል። እንዲሁም ጥቃት የደረሳቸው ሴቶችና ህፃናት ማረፊያዎችንና ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ ህፃናት ማቆያ ተቋማትን በተመሳሳይ ሁኔታ በመፈተሽ የተለያዩ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፎችን ማድረግ ተችሏል።

ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ከመከላከልና ከማስወገድ አንፃር በየደረጃው ለሚመለከታቸው አካላት ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ የሃይማኖት አባቶች፤ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሴቶችና የወጣቶች አደረጃጀት አመራሮች፣ የልጃገረዶች ፎረም መሪዎች፣ የትምህርት ቤቶች ክበባት መሪ መምህራንና ተማሪዎች በየደረጃው በማሳተፍ በቅንጅት እየተሠራ ይገኛል።

በሌላ በኩል የሴቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሣትፎን ከማረጋገጥ አንፃር በንቅናቄው ሂደት የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ በየደረጃው በመሥራት ሴቶች በከተማ ውበትና ጽዳት ሥራ፣ አቅመ ደካሞችን ለመርዳት ሀብት የማሰባሰብ ሥራ ወዘተ ተግባራት 2,931,282 ሴቶችን እንዲሳፉ ማድረግ ተችሏል።

በተመሳሳይ በሴቶች ከሚሰሩ በጎ አድራጎት አገልግሎቶች ውስጥ አንዱ ከሆነው የደም ልገሳ ከታቀደው በላይ 7,144 ዩኒት ደም መሰብሰብ ተችሏል።

ከዚህ በተጨማሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሴቶችን ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ ሀገራዊ ፕሮግራሞች እንዲቀረጹ በማድረግ ረገድ ከአጋር አካላት ጋር የተለያየ የምክክር መድረኮች በማዘጋጀት በተለይ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በገባው ስምምነት የሴቶችን የኢኮኖሚ አቅም ለማጎልበትና ምንዳ በቤተሰብ ደረጃ እንዲያፈሩ ለማስቻል ምንዳ ለሴቶች በሚል መርህ በየክልሉ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት በ15,000,000 ብር ወጪ ለተመረጡ 500 እማወራ ሴቶች የልብስ ስፌት መኪና ድጋፍ የሚያገኙበት ሁኔታ መመቻቸቱ የማርች 8 በዓልን ምክንያት በማድረግ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል በዋናነት ተጠቃሽ ሲሆን በዚህ አጋጣሚ ኢትዮ ቴሌኮም ላደረገው ድጋፍ በኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በተጠቃሚ እህቶቻችን እና በራሴ ስም ከፍ ያለ ምስጋናችንን ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡

በዚህ አጋጣሚ ለእቅዱ መሳካት የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከታችሁ የክልልና የከተማ አስተዳደሮች በተለይ ለክልል ቢሮዎቻችን እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻና አጋር አካላት በሙሉ በድጋሚ በሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ስም ከልብ እያመሰገንኩ በእቅድ የያዝናቸውና የተጀመሩ ቀሪ ተግባራት እስከ መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ተጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል። በዚህም የተለያዩ ድጋፎችን ይፋ የምናደርግ ይሆናል።

በመሆኑም ሂደቱን የመከታተል፣ የማስተባበርና የመደገፍ ስራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው አደራ ለማለት እወዳለሁ፡፡

በመጨረሻም ወቅታዊ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ይህን ፕሮግራም በቀጥታ ስርጭት ተደራሽ በማድረግ ስለተባበረን ከልብ ለማመስገን እንፈልጋለን፡፡

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
አመሰግናለሁ!

Please follow and like us: