“የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ውጤታማነትንና የዜጎችን የተሻለ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ዘርፉን በእውቀት መምራት ያስፈልጋል” – አቶ ተስፋዬ ሽፈራው

በፕሮግራሙ በቋሚና በጊዜያዊ የቀጥታ ድጋፍ የሚሠጡ አገልግሎቶችን ውጤታማነትን እና የዜጎችን የተሻለ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያለመ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል።

በስልጠና መርሀ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ጥበቃ፣ ማስተባበሪያና መከታተያ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ ሽፈራው በልዩ ልዩ ምክንያቶች ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑትን የገጠር የህብረተሰብ ክፍሎች ከድህነት ለማላቀቅና ሁለንተናዊ ደህንነታቸው እንዲረጋገጥ ለማስቻል ፕሮጀክትና ፕሮግራም ተነድፎ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል። በእስካሁን የፕሮግራሙ ትግበራ በገንዘብ ድጋፍና በመሰረታዊ የማህበራዊ አገልግሎቶች ትስስር መፍጠር ረገድ መጠነ ሰፊ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል። በዚህም በርካታ ወገኖችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል።

ሆኖም ፕሮግራሙ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ፣ ቀጣይነት እንዲኖረው እንዲሁም ዜጎችም የተሻለ ተጠቃሚነት እንዲሆኑ ለማስቻል ዘርፉ በእውቀት ሊመራና የተጀመሩ ስራዎችም ይበልጥ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል። ለዚህም የፕሮግራም አስተግባሪ አካላት የበለጠ ትኩረት እንዲሰጡና በቅንጅት እንዲሰሩም ኃላፊው አቶ ተስፋዬ ሽፈራው ጥሪ አቅርበዋል። ስልጠናው በማስፈጸም ረገድ የሚስተዋሉ ጉድለቶችን ለመቅረፍ ያለመ ነው ያሉት ኃላፊው ሰልጣኞች በስልጠናው ያገኙትን ክህሎት በአግባቡ በስራ ላይ እንዲያውሉም አሳስበዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።

ስልጠናው በዋናነት መሠረታዊ የማህበራዊ አገልግሎት ትስስርን በማጠናከር፣ በማህበራዊና ስነልቦናዊ ድጋፍ አገልግሎት አሰጣጥ እንዲሁም በጉዳይ አያያዝ ዙሪያ ባሉ የአሰራር ማዕቀፎች ላይ ያተኮረ ነው። በስልጠና መርሀ ግብሩም ከኦሮሚያ፣ ከሲዳማ፣ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ፣ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች የተውጣጡ የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ጽ/ቤት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛል።

 

Please follow and like us: