የአካል ጉዳተኞችን መብት እንደማንኛውም ዜጋ ማክበር አካል ጉዳተኞች በህዝብ አገልግሎቶችና ዕድሎችን እኩል ተደራሽና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለሚደረገው ድጋፍ መሰረት መሆኑ ተገለፀ ።

ይህ የተገለፀው የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢንክሉዥን ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በተ.መ.ድ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮንቬንሽንና ሌሎች አካል ጉዳተኛን የተመለከቱ የህግ ማዕቀፎች ላይ ለፌደራል አስፈፃሚ መ/ቤቶች የአቅም ግንባታ ስልጠና በሰጠበት ወቅት ነው።

በመድረኩ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ አሳልፈው አመዲን እንደገለፁት አካል ጉዳት የእለት ተእለት ክስተትና አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል። የአካል ጉዳት በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ ምክንያት ከተከሰተ በኃላ የአካል ጉዳተኞችን መብት እንደማንኛውም ዜጋ ማክበር አካል ጉዳተኞች በህዝብ አገልግሎቶችና ዕድሎችን እኩል ተደራሽና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለሚደረገው ድጋፍ መሰረት እንደሚሆን ጠቅሰዋል ።

ለዚህም መንግስት የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተ.መ.ድ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮንቬንሽን ያወጣቸው ህጎች ከመቀበል አንስቶ ሌሎች የህግ ማዕቀፎችና መመሪያዎች እስከታችኛው የመንግስት መዋቅር ድረስ ተግባራዊ መሆናቸውንና መንግስት አካል ጉዳተኞችን ማካተትና ማሳተፍ ላይ ትኩረት እድርጎ እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል። ስራ አስፈጻሚው አክለውም የአካል ጉዳተኞች የመብት ጥሰት ለመከላከል እና እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እንዲቻል ይህ አይነቱ ስልጠና አስፈላጊነቱን ገልፀዋል ።

ከኢንክሉዥን ኢትዮጵያ አቶ ዮሴፍ ፍቃደ በበኩላቸው
በኢትዮጵያ ለአካል ጉዳተኞች የሚመጥን መሠረተ ልማት አውታር ግንባታ አለመኖር እና አገልግሎት አሰጣጥ ጉድለት በርካቶችን ለከፍተኛ እንግልት እና የጤና ችግር እንደዳረጋቸው ገልጸዋል ።

ተቋማቸውም ይህንን መሰል ችግሮች ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል ። በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ አካል ጉዳተኛ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ቁጥር  ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል፡፡  ቁጥሩ ከአንድ ቢሊዮን በላይ እንደሚሆን ይገመታል፡፡

ይህ ቁጥር በዓለም ላይ ባሉ በርካታ ሀገራት ከጠቅላላው የህዝብ ብዛት 15.3 ከመቶ እንደሚይዝ እና በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ደግሞ ከ15-20 ከመቶ እንደሚደርስ የዓለም ባንክ እንደ እ.ኤ.አ 2011 በአካል ጉዳተኝነት ላይ ያወጣው መረጃ  ያሳያል።

Please follow and like us: