በሥርዓተ-ፆታ እኩልነት እና በሴቶች ልማት ላይ እየመከረ ባለው 68ኛው አለም አቀፍ ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ ልዑካን እየተሳተፉ ይገኛል

“ድህነትን በመቅረፍ፣ ተቋማትን በማጠናከርና በሥርዓተ ፆታ እይታ ፋይናንስን በማጎልበት የሥርዓተ ፆታ እኩልነት ስኬትን ማፋጠን እና ሁሉንም ሴቶችና ልጃገረዶች ማብቃት” በሚል መሪ ቃል ከማርች 11-22 ቀን 2024 ዓ.ም እየተካሄደ ባለው 68ኛው ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ ልዑካን እየተሳተፉ እንደሚገኙ ልዑካን ቡድኑ በሪፖርታቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን በመወከል በጉባኤው ለመታደም ከኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከገንዘብ ሚኒስቴር የተወጣጡ ባለሙያዎችን ያቀፈ ልዑካን ቡድን ወደ ኒውዮርክ ማቅናቱንና በኦፊሴላዊው የስብሰባ አጀንዳ በተመረጡ ርእሰ ጉዳዮች እና የጎን ለጎን ምክክሮች ላይ በንቃት እየተሳተፈ መሆኑንም ገልፀዋል። የልዑካን ቡድኑ አባላት “ለጾታ እኩልነት ሀብትን ማሰባሰብ፣ የሴቶችን እና ልጃገረዶችን ማብቃት እንዲሁም የሴቶች እና የታዳጊ ሴቶች ድህነት ለማስቀረት የፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች” በሚል መሪ ሃሳብ እ.ኤ.አ. መጋቢት 12 እና 13 ቀን 2024 በተካሄደው የሚኒስትሮች ምክክር መድረክ የመከፈቻ ፕሮግራም እና የውይይት መርሀ ግብር ላይ ተሳትፏል ብለዋል። በተመሳሳይ “የሥርዓተ ፆታ እኩልነትን ለማስፈን እና ሁሉንም ሴቶች እና ልጃገረዶች ለማብቃት ተቋማትን በማጠናከር እና የገንዘብ ድጋፍን በማሳደግ ረገድ ያሉ መልካም ተሞክሮዎች” በሚል በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይም ተሳትፎ መደረጉን ጠቁመዋል።

በተለይ ስርዓተ ጾታ ፈይናንሲግ እና በጀት፣ ጾታዊ ጥቃት ምላሽ አሰጣጥ፣ የሥርዓተ ፆታ፣ ሴቶች እና ልጃገረዶች መረጃ አደረጃጀትና ትንተና፣ ስርዓተ ጾታ እና ማህበራዊ ጥበቃን በተመለከቱና GAGE ባዘጋጀው መድረክ ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ መቻሉን ነው የገለጹት፡፡

በሌላ በኩል በዩኒሴፍ እና በዩኤንኤፍፒኤ የጋራ ትብብር የሚካሄድና የህጻናት ጋብቻ ማቆም ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ አገራት በቀጣይ አምስት ዓመታት የሚተገበር ሶስተኛው ዙር ፕሮግራም ይፋ በተደረገበት መድረክ ላይም ልዑካኑ መሳተፋቸው ተመልክቷል፡፡ የሀገራት ሪፖርት በሚቀርብበት ዋናው ፕሮግራም ላይም በመገኘት የኢትዮጵያን ሪፖርት በተሳካ ሁኔታ ማቅረብ እንደተቻለም ገልጸዋል፡፡ ቡድኑ በተለያዩ አባል ሀገራት፣ አለም አቀፍ ድርጅቶች እና የሲቪክ ማህበራት ባዘጋጁት መድረኮች ላይ መሳተፍ መቻሉ ጠቃሚ ተሞክሮዎችን ለመውሰድ መልካም አጋጣሚ እንደፈጠረላቸው ገልፁዋል።

መድረኩ እ.ኤ.አ በ2019 “የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓቶች፣ የህዝብ አገልግሎቶች ተደራሽነት እና ዘላቂነት ያለው መሠረተ ልማት ለሥርዓተ-ፆታ እኩልነት እና የሴቶች እና ልጃገረዶችን ማብቃት” በሚል መሪ ቃል በተካሄደው 65ኛው ጉባኤ የተወሰኑ ውሳኔዎች ያሉበትን የአፈጻጸም ደረጃ እንደሚገመገም የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በአለም አቀፍ ደረጃ በሥርዓተ-ፆታ እኩልነት እና በሴቶች ልማት ላይ ትኩረት ያደረገና CONVENSION ON THE STATUS OF WOMEN (CSW) በመባል የሚታወቀው ዋና ዓለም አቀፍ ፖሊሲ አውጪዎች የሚሳተፉበት የጉባኤ መድረክ በየአመቱ እንደሚካሄድ ይታወቃል፡፡

 

 

Please follow and like us: