በዕድል የመጠቀም ትግልና ውጤት

ያኔም ሆነ ዛሬ ከወንድ እኩል መምራት እና ማስተዳደር የሚችሉ ብቃት ያላቸው ሴቶች በኢትዮጵያ ነበሩ፤ አሉ። ዛሬም ሆነ ትላንት እኩልነታቸውን የሚገዳደር አመለካከት ነበር፤ አለም። አሁን ላይ በብዙ መልኩ እየተለወጠ ይምጣ እንጂ ይብዛም ይነስም የትላንቱ አመለካከት በዛሬው ትውልድ ላይ መጫኑ አልቀረም፡፡ ሴቶች ጫናውን ከራሳቸው ላይ በማራገፍ ዘመኑ የሰጣቸውን ዕድል ለመጠቀም ብርቱ ጥረትና ትግል ማድረጋቸውም አልቀረም፡፡

ጡረተኛዋ መምህርት ወይንአበባ አሰፋ ለዚህ ብርቱ ጥረትና ትግል እንደአብነት ከሚጠቀሱ ሴቶች አንዷ ናቸው። በ1949 ዓ.ም ተወልደው ያደጉት በድሮው ወሎ ክፍለ ሀገር ደሴ ከተማ ነው። የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም እዚያው በሚገኙት የወይዘሮ ስህንና ንጉስ ሚካኤል ትምህርት ቤቶች አጠናቅቀዋል። በተለያዩ የትምህርት መስኮች ዲግሪዎች አሏቸው። ለዚህም የበቁት ስድስት ልጆች ከወለዱና 16 የልጅ ልጆች ካዩ በኋላ ነው። ይሄኛው የስኬት ታሪካቸው ትግላቸውና ጥረታቸው ትምህርታቸውን ከ10ኛ ክፍል አቋርጠው ከ20 ዓመት በላይ ለሚበልጣቸው ባል ከተሰጡበት ጊዜ ይ ጀምራል። ወይዘሮ ወይንአበባ የታጨላቸውን ባል አሻፈረኝ በማለት ከልጅነት ፍቅረኛቸው ጋር ወደ አዶላ ኮበለሉ። በ18 ዓመታቸው የመጀመሪያ ልጃቸውን ለ45 ዓመት አብረዋቸው በአንድ ጣራ ከኖሩት የዛሬው የትዳር አጋራቸው ወለዱ። ከአዶላ ወደ ደሴ ተመለሱ። ከ10ኛ ክፍል ያቋረጡትን ትምህርታቸውንም ቀጠሉ። ዕድገት በሕብረት ዘምተው ፊደል ብቻ ሳይሆን በትዳር ስም እንደሳቸው ጫና የሚደረግባቸው ሴቶች እንቢኝ እንዲሉም አስተማሩ። የመረጡትን ከማግባት አልፈው ስድስት ልጆችና 16 የልጅ ልጆች ካዩ በኋላ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግብተው ተማሩ፡፡ ከ40 ዓመት በላይ በመምህርነት ሙያቸው በተለያዩ ኃላፊነት ቦታዎች ለማገልገል በቁ። በጥረታቸውና ትግላቸው ገና በጠዋቱ ከባል ጥገኝነት ራሳቸውን አላቀቁ፤ አሁን በጡረታ ላይ ሆነው እንኳን የተለያዩ የቴሌቪዥን ፊልም ማስታወቂያዎችን በመሥራት ገቢ ለማግኘትም በቁ።

ሌላኛዋ ባለታሪክ ጋዜጠኛ ሂሩት ተፈራ ትባላለች፡፡ በትግሏና በጥረቷ መብቷን ያስከበረች ጀግኒት ናት። ተወልዳ ያደገችው በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ሲሆን 18 ዓመት የጋዜጠኝነት ሙያ ልምድ አላት። ሬዲዮ ፋና ከሰራችበት የመገናኛ ብዙኃን ሲጠቀስ በአሁኑ ወቅት በቢቢሲ ሚዲያ አክሽን በአርታይነት እየሠራች ትገኛለች። የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷንም ተወልዳ ባደገችበት ነው የተማረችው። የከፍተኛ ትምህርቷን በጋዜጠኝነት ሙያ ቀድሞ የኢትዮጵያን ማስ ሚዲያ ትሬሊንግ ሴንተር በሚባለው አሁን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት አጠናቃለች። ይሄን ዕድል የሰጣት ደግሞ ተወልዳ ያደገችበት የሶማሌ ክልል ሲሆን ዕድሉ የመጣው በክልሉ ትምህርት ቢሮ ነበር። የተሰጠውን ዕድል ለመጠቀም ሴትነቷ ሳይበግራት ብርቱ ትግልና ጥረት አድርጋ አሰበችው ቦታ ደርሳለች፡፡ ሂሩት ዛሬ የደረሰችበት ቦታ ላይ ለመድረስ መንገዶች ሁሉ አልጋ በአልጋ አልነበሩላትም ፤ ሴትነቷን ምክንያት አድርገው የተጋረጡ በርካታ ጋሬጣዎችን አልፋለች፡፡ በተለይም ተውልዳ ባደገችበት አካባቢ ቀደም ሲል ለሴቶች ይሰጥ የነበረው አመለካከት እርሷንም ክፉኛ እንደፈተናት ታስታውሳለች፡፡ የወጣውን መመዘኛ መስፈርት ተወዳድሮ ለማለፍ፣ ውድድሩን አልፋ ተምራ ስትመለስም ምድብ ቦታ ለማግኘት፣ ተመድባ እየሰራችም ቢሆን በተመደበችበት ቦታ ላይ የሚከፈለውን ደመወዝ ለማግኘት ሴት መሆኗ ብቻ ብዙ አመኔታ እንዳሳጣት ትናገራለች፡፡ ሂሩት ሁሉንም የሴትነት ጫናዎች በጥረቷ ተሻግራ ዛሬ ላለችበት ደረጃ በቅታለች፡፡ ይሄ የእርሷና የሌሎች ሴቶች ትግል በክልሉ ውጤት ማምጣቱንና ዛሬ በሚኒስትር፤ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግና በሌሎች ከፍተኛ ኃላፊነቶች ላይ ብዙ ሴቶች እንዲወጡ ያስቻለ፤ ኋላቀር አስተሳሰብን የለወጠ የትግል አስተዋጽኦ ማበርከቷን ትናገራለች፡ ፡ የግል ጥረትና ትግል ወሳኝ በመሆኑ ሴቶች በሴትነታቸው የሚደርሱባቸውን ጫናዎች ሁሉ ተቋቁመው ያሰቡት ቦታ ለመድረስ ሁሌም ብርቱ ጥረትና ትግል ማድረግ እንዳለባቸውም ትመክራለች።

እንዲህ ዓይነቱ የሴቶች ትግልና ጥረት እጅግ አስፈላጊ ስለመሆኑ ወይዘሮ ማስተዋል ሞሴ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአረጋዊያን ጉዳዮች መብት ጥበቃና አድቮካሲ ባለሙያ ይናገራሉ። በተለይም ኋላቀር አስተሳሰብ በሚንጸባርቀበትና በርካታ ሴቶች በሚኖሩበት የገጠሪቱ ኢትዮጵያ አካባቢ ተሞክሮውን ማስፋትና ያላሰለሰ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ማከናወንም እንደሚገባ ያሳስባሉ። ‹‹…አመጣጤ ገጠር ስለሆነ ያለውን ችግር እረዳዋለሁ…›› የሚሉት ባለሙያዋ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው ከተማ ላይ ሳይገደቡ እንደ ሴቶች ቀን ያሉትን በዓላት ጭምር ወጣ ብሎ ገጠር በማክበር፤ ሴቶች ከወንዶች እኩል የትምህርት፤የሥራና ሌሎች ኃላፊነቶችን ቦታ እንዲያገኙ ከወንድና ሴት ልጅ አስተዳደግ ጀምሮ ታች ወርዶ ስልጠና መስጠት እንደሚያስፈልግም ያነሳሉ። ሴቶች ከጓዳ እንዲወጡና፤ የተሻለ ዕድል እንዲያገኙ ግንዛቤ መፍጠር፤ ሰላም ማምጣት አስፈላጊ ነው፤ ስለ ሰላም ስለልጆቻችን አስተዳደግ በትክክል መሥራት አለብን፤ ሴቶች የልጆቻችንን ባህርይ ማወቅ አለብን፤ ወደ ጥፋት በሚሄዱ ጊዜ የመመለስ ትክክለኛውን አቅጣጫ የማሳየት ኃላፊነትም የእኛ ነውና ሴቶች በተረጋጋ አካባቢ፤ መኖር ማደግ ሲችሉ የሚያይዋቸውን፤ የሚሰሟቸውን ጥሩ ነገሮች እየወሰዱ ወደ ተሻለ ሕይወት እንዲገቡ ማስቻል አስፈላጊ ስለመሆኑም በመግለጽ ሃሳባቸውን ያሳርጋሉ።

Please follow and like us: