ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ በጦርነት ምክንያት በንግድ ስራቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸውን 1ሺህ ሴቶች ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

‘Rebuild Her Business’ የተሰኘና በትግራይ፣ በአፋር እና በአማራ ክልሎች በጦርነት ምክንያት በንግድ ስራቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸውን 1ሺህ ሴቶች ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችል የ22 ሚሊዮን 149ሺህ 522 ብር ፕሮጀክት ይፋ ሆኗል።

ፕሮጀክቱ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተባባሪነት በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ እና በዩ ኤን ዲ ፒ አማካኝነት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚተገበር ተገልጿል። የፕሮጀክት የመግባቢያ ስምምነት የፊርማ ስነስርዓቱን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ኤርጎጌ ተስፋዬ እንዲሁም በኢትዮጵያ የዩ ኤን ዲ ፒ የፕሮግራም ኃላፊ ሚስተር ሳሙኤል ዶይ አካሂደዋል። በዚሁ ጊዜም፥ ሚኒስትር ክብርት ኤርጎጌ ተስፋዬ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በነበረው ጦርነት ምክንያት አነሰተኛና መካከለኛ የንግድ ስራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ሴቶች ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል። ፕሮጀክቱ ሴቶች በተለያዩ የገቢ ማስገኛ መስኮች በመሰማራት የኢኮኖሚ አቅማቸውን ከማሳደግ በተጨማሪ ወደ ቀደመ ህይወታቸው እንዲመለሱና በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

የገንዘብ ድጋፉ ባለፋት ስድስት ወራት መሰብሰቡንና ወደፊትም ቀጣይነት እንደሚኖረው ገልጸዋል። ሃሳቡን ከማመንጨት ጀምሮ ሀብት በማሰባሰብና ፕሮጀክቱ እውን እንዲሆን ሰፊ ስራ በመስራት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ላሉ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ፣ ዩ ኤን ዲ ፒ፣ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ፣ የጀፓን መንግስትና ሌሎች አካላት በተጠቃሚ ሴቶች ስም ምስጋና አቅርበዋል።ፕሮጀክቱ በመንግስትና በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መካከል ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከርና በጋራ አብሮ መስራት ከተቻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ትልቅ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ዳግማዊት አማረ በበኩላቸው በተለያዩ ጊዜያት ማህበራዊ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው ይህም ፕሮጀክት ሴቶች ከራሳቸው ባለፈ ቤተሰባቸውና ማህበረሰባቸውን ለመደገፍ የሚያደርጉትን ጥረት ያግዛል ብለዋል። በዕለቱ ከተለያዩ አካላት ያሰባሰበውን የገንዘብ ድጋፍም ስራ አስኪያጇ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስረክበዋል። በፕሮጀክቱ የሚታቀፉ ሴቶች የማህበረ ስነልቦናዊ ድጋፍና የንግድ ክህሎት ስልጠና እንዲወስዱ የሚደረግ ሲሆን በመጀመሪያው ዙርም 775 ሴቶችን ስራ ለማስጀመርና ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ለእያንዳንዳቸው የ500 ዶላር ድጋፍ እንደሚደረግ በስነስርዓቱ ላይ ተጠቅሷል።

Please follow and like us: