“ለችግር ተጋላጭ ዜጎችን ሁለንተናዊ ደህንነት ለማስጠበቅና በዘላቂነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ጠንካራ የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል” – አቶ ተስፋዬ ሽፈራው

በከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ስራ ፕሮጀክት በቋሚና በጊዜያዊ የቀጥታ ድጋፍ የሚሠጡ አገልግሎቶችን ውጤታማነትን እና የዜጎችን የተሻለ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያለመ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል።

በስልጠና መድረኩ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ጥበቃ፣ ማስተባበሪያና መከታተያ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ ሽፈራው ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑትን የህብረተሰብ ክፍሎችን ከድህነት ለማላቀቅና ሁለንተናዊ ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጁዎችንና ፕሮጀክቶችን ነድፎ ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ስራ ፕሮጀክት በዋነኝነት ይጠቀሳል ያሉት ኃላፊው ፕሮጀክቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ መተግበር ከጀመረበት ከ2008 ዓ.ም ወዲህ የገንዘብ ድጋፍና መሰረታዊ የማህበራዊ አገልግሎቶች ትስስርን በመፍጠር ረገድ ሰፋፊ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል። በዚህም በርካታ ወገኖችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል። ይሁንና አሁንም በመረጃ አያያዝና ልውውጥ፣ ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር፣ በክትትልና ድጋፍ እንዲሁም ዘርፉን በእውቀት ከመመራት አንጻር  ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቁመው የአስፈጻሚ አካላትን አቅም ለማጎልበት ስልጠናው መዘጋጀቱን አስገንዝበዋል። ለችግር ተጋላጭ ዜጎችን ሁለንተናዊ ደህንነት ለማስጠበቅና በዘላቂነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል እንደሀገር ጠንካራ የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል።

ለዚህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸው በመተግበር ላይ ያለው ፕሮጀክት የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ፣ ቀጣይነት እንዲኖረው እና ዜጎችም ከዘርፉ የተሻለ ተጠቃሚነት እንዲሆኑ ለማስቻል የክልልና የከተማ አስተዳደር መዋቅሮችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በቅንጅት እንዲሰሩም መሪ ስራ አስፈጻሚው ጥሪ አቅርበዋል:: ውጤታማ የፕሮጀክት አፈጻጸም እንዲመዘገብ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።

ስልጠናው በዋናነት ደህንነቱ የተረጋገጠ የማህበራዊ ጥበቃ አሰራር ስርዓት በመዘርጋት፣
መሠረታዊ የማህበራዊ አገልግሎት ትስስርን በማጠናከር፣ በጉዳይ አያያዝና የስርዓተ ጾታና ማህበራዊ ልማት ማስፈጸሚያ ማኑዋል ዙሪያ ባሉ የአሰራር ማዕቀፎች ላይ ያተኮረ ሲሆን በስልጠና መርሀ ግብሩ ከሁሉም ክልልና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛል።

Please follow and like us: