የተቋሙ አመራሮች በልደታ ክፍለ ከተማ ለሚገኙ አቅመ ደካማ ነዋሪዎች ማዕድ የማጋራት መርሀ ግብር አካሄዱ

የተቋሙ አመራሮች የረመዳን እና የአብይ ጾምን ምክንያት በማድረግ በልደታ ክፍለ ከተማ ለሚገኙ አቅመ ደካሞች ማዕድ የማጋራት መርሀ ግብር አካሂደዋል።

በመርሀ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እና የማህራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊን ጨምሮ የክፍለ ከተማው አመራሮችና ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

በዚሁ ጊዜ፥ የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ባስተላለፉት መልዕክት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችንና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አቅመ ደካማ ወገኖችን ለመደገፍና በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ለማስቻል በርካታ ስራዎችን በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ህብረተሰቡና የበጎ አድራጎት ተቋማትም አቅም በፈቀደ መጠን በዝቅተኛ ኑሮ ላይ የሚገኙ ወገኖችን በመርዳት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ሚኒስትሯ ጥሪ አቅርበዋል።

የማህራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታና የልደታ ክፍለ ከተማ ተመራጭ ክብርት ሁሪያ አሊ በበኩላቸው እንደሀገር ችግር በገጠመን ወቅት አንዳችን ላንዳችን እየተደጋገፍን እዚህ ደርሰናል፤ ወደፊትም አብረን ከሰራን፣ ከተደጋገፍንና ከተረዳዳን የማንሻገረው ችግር የለም ብለዋል።

በተለይ ወቅቱ ታላቅ የጾም ጊዜ እንደመሆኑ መጠን አቅመ ደካማ ወገኖች ጾሙንም ሆነ በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ መደጋገፍን ማዕከል ያደረገው በጎ እሴታችን ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርብናል ብለዋል።

የክፍለከተማው መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰዒድ አሊ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው አስተዳደሩ ሰው ተኮር የሆኑ ስራዎችን ይበልጥ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ፕሮግራሙን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።

Please follow and like us: