“የሴቶችን የስራ ጫና ለመቀነስ እና የህጻናትን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ በተቋማት አካባቢ የህጻናት የቀን ማቆያዎችን ማስፋፋትና ማጠናከር ይገባል” – (ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ)

በይርጋለም ጋርመንት እና ኢትዮኢምፓክት አምራች ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የተገነቡ የህፃናት ማቆያ ማዕከላት የምረቃ ስነ-ስርዓት ተካሂዷል፡፡

በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ ባስተላለፉት መልዕክት፥ በመንግስት ተቋማትም ሆነ በአምራች ኢንዱስትሪዎች አካባቢ ምቹ የስራ ሁኔታ ለመፍጠር፣ የሴቶችን የስራ ጫና ለመቀነስ ብሎም የህጻናትን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ ደረጃቸውን የጠበቁ የህጻናት የቀን ማቆያዎችን ማስፋፋትና ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

የማቆያዎቹ መገንባት ሴት ሰራተኞችን አምራች፣ ተቋማትንም ውጤታማ ሲያደርግ ህፃናት እና ቤተሰቦቻቸውም የተሻለ ህይወት እንዲኖራቸው ያስችላል ብለዋል።

 

 

በዚህ ረገድ የተጀመሩ ጥረቶችን ሚኒስትር ዴኤታዋ አድንቀው ሆኖም እንደሀገር ካለው ችግር አንፃር ተደራሽነቱን ይበልጥ ለማስፋፋትና ለማጠናከር እንዲያስችል የወጣው አዋጅ ቁጥር 1064/2010 ዓ.ም ተፈጻሚ እንዲሆን አሁንም ትኩረት መስጠትና በቅንጅት መስራት እንደሚገባ በአጽዕኖት አሳስበዋል፡፡

የኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚንስትር ደኤታ አቶ ሀሰን መሀመድ በበኩላቸው በአምራች ኢንዱስትሪዎች የህፃናት ማቆያ ማዕከላት መኖር ለሴት ሰራተኞች ምቹ የስራ ከባቢ ከመፍጠር ባሻገር ባለሙያዎቹ ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው እንዲሰሩ በማድረግ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳው የጎላ እንዲሆን ያደርገዋል ብለዋል፡፡

 

አቶ ሀሰን ሙሀመድ አክለውም በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰማሩ ሴት ሰራተኞችን አቅም ከማጎልበትና ምቹ የስራ ሁኔታን ከመፍጠር አኳያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠንክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

Please follow and like us: