ሙያዊ ክብርን ለመጎናጸፍ – ስነ ምግባርን መርህ ያደረገ አገልግሎት

ዜጎች በየተሰማሩበት የስራ መስክ ተልዕኮዋቸውንና አገራዊ ግዴታቸውን በቅንነት፤ በታማኝነትና በቆራጥነት ሲፈጽሙ ሙያዊ ስነምግባራቸውን ሲያከብሩ፣ ለኅሊናቸው ታዛዥና ለህግ ተገዥ ሆነው ሲገኙ የበለጸገች አገር ይኖራቸዋል። ይህ ደግሞ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው ዜጎች የስነምግባር ትምህርትን በመማራቸውና በማወቃቸው ብቻ ሳይሆን የተማሯቸውንና ያወቋቸውን የጥሩ ስነምግባር መገለጫዎች በተግባር በማሳየታቸው፣ የእለት ተእለት ልምዳቸው በማድረጋቸው ነው። በአንጻሩ ደግሞ የመጥፎ ስነምግባር መገለጫ የሆኑትን ተግባራት ላይፈጽሙ ለራሳቸው ቃል በመግባታቸውና የተግባር ሰው ሆነው በመገኘታቸው ነው። በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት ተቋማት ህብረተሰቡን በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል የተዋቀሩ በመሆናቸው ለእውነተኛ እና ትክክለኛ አገልግሎት የቆሙ መሆኑን ተገልጋዩ የማህበረሰብ ክፍል የሚረዳው ባለሙያዎቹ በሥነምግባራቸው ምስጉን ሆነው ሲገኙና   አገልጋይነት ሙያዊ ክብር የሚያስገኝ መሆኑን ተረድተው በተሰማሩበት ዘርፍ ፈጣን፣ ቀልጣፋና ተደራሽ  የሆነ አገልግሎት ሲሰጡ ነው።

በአንድ መድረክ ላይ የማህበረሰብ አባላትን ሲያሰለጥን የነበረ አንድ ባለሙያ ስነምግባር ምንድን ነው ብሎ ይጠይቃቸዋል:: ከሰልጣኞች ከተሰጡት ምላሾች መካከል አንደኛው “ ስነ ምግባር ማለት ስሜቴ ትክክል ነው የሚለኝን መፈጸም ነው “ በማለት ይመልሳል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ “ ስነ ምግባር ማለት ኃይማኖቴ የሚመራበትን መፈጸም ነው” የሚል ነበር። ቀጣዩ ምላሽ ሰጪ “ ስነ ምግባር ማለት ህጉ የሚለውን መፈጸም ነው “ ሲል ተከታዩ ደግሞ “ስነ ምግባር ማህበረሰብ የተቀበላቸውን የባህሪ መስፈርቶች መከተልና መፈጸም ነው።” የሚሉ ነበሩ። ሁሉም ተሳታፊዎች የሰጡት ምላሽ እንደተጠበቀ ሆኖ የጋራ ልናደርገውና ወደሚገባን ትርጓሜ ስናመራ ስነ ምግባር የሰው ልጆችን ባህሪና ድርጊት የሚያጠና፣ የጥሩና መጥፎ ባህሪ መመዘኛ፣ የትክክልና ስህተት መለኪያ፣ የመልካም ባህሪ መግለጫ፣ የባህሪ መለኪያ መርሆዎች ስብስብ፣ እንዲሁም በአገልግሎት አሰጣጥ ውስጥ ስለ ትክክልና ስህተት፣ ማድረግ ስለሚገባንና ስለማይገባን፣ ስለጥሩና መጥፎ ተግባር የሚናገር መሆኑን በስነምግባር ዙሪያ ጥናት ያደረጉ ምሁራን ያመለክታሉ፡፡

የስነ ምግባር ትርጓሜን ከመንግስት ስራ ጋር ስናያይዘው ጥሩ ውሳኔ የመወሰንና ለሌሎች አርአያ የመሆን ሂደት (process) ፣ አስተዋይ ሆነን አማራጮችን አይተንና ገምግመን ውሳኔ የመወሰን ሂደት፣ በአገልግሎት ውስጥ ትክክለኛውን ለማድረግ እንቅፋት የሆኑ ነገሮችን እንድናይና እንድናስወግድ የሚጠይቅና ስራችንን ከመርህና ከህግ አንጻር እንድናከናውን የሚያስገነዝብ ነው። ስነምግባር ጥሩ እና መጥፎ፣ በጎ እና ክፉ ሀሳብ፣ ንግግር እና ድርጊትን የሚገልጽ ስርአት ሲሆን አንድን ሀሳብ ወይም ድርጊት መልካም ወይም መጥፎ፣ ትክክል ወይም ስህተት፣ ዋጋ ያለው ወይም የሌለው፣ ፍትሀዊ ወይም ኢፍትሀዊ መሆኑን ለማረጋገጥ የሚጠቅም መለኪያ ነው። ማንኛውም የመንግስት ሰራተኛ በግልም ህይዎት ይሁን በመንግሥት ተቋም ውስጥ አገልግሎት ሲሰጡ ሊከተሏቸው የሚገቡ መርሆዎችና እሴቶች እንዳሉም መረዳት ያስፈልጋል።

እነዚህ መርሆዎች ሁሉን አቀፋዊና “አስገዳጅ” የሆኑ የትክክለኛ የባህሪ አቅጣጫ አመልካቾች ናቸው። ዘርን፣ ቀለምን፣ ሃይማኖትን፣ ልማድን ወይም አመለካከትን መሰረት አድርገው በሰዎች መካከል ልዩነት የማይፈጥሩ ናቸው። እሴት ስንል በአንድ ግለሰብ ውስጥ ያለ ጥሩና ትክክለኛ ባህሪን የመላበስ ፈቃደኝነትንና ምኞትን የሚገልጽ ነው። መርህ ደግሞ ልጓም፣ እሴት ደግሞ ፈረስ ማለት ነው። ሁለቱም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። ስለዚህ የመንግስት ሰራተኞች ከላይ የተዘረዘሩትን ተግባራት በመፈጸም ውጤታማ እንዲሆኑ የስነምግባር መመሪያውን ወይም የስነምግባር ደንቡ በሚያዘው መሰረት መተግበር ይጠበቅባቸዋል።

በዚህ መሰረት በማንኛውም ተቋም ውስጥ የሚገኙ ሠራተኞች ግላዊ፣ ሙያዊና ተቋማዊ የተሰኙ ሶስት መሠረታዊ ሥነ-ምግባሮች እንዲከተሉ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፤ ግላዊ ስነምግባር አንድ ሰው ከቤተሰቡና ከአካባቢው ማህበረሰብ ይዞት አዳብሮት የሚያሳድገው ግላዊ ባህሪ ነው። ይህ የሥነ-ምግባር ዓይነት ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው እና ሁሉም የሰው ልጆች ሊኖራቸው የሚገባ ነው። በግል ህይወታችን ውስጥ ሥነምግባርን የምንለካው በቃል አክባሪነት፣ በሰው ወዳድነት፤ በሐላፊነት ስሜት፣ በተዓማኒነት፣ በጠንካራ ሰራተኛነት፣ በትጋትና በግልፅነት ሲሆን፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ እምነትና ተስፋ የሚጣልበት ሰው ከመሆን አንፃር የሚታይ ነው።

ሙያ በልዩ ትምህርታዊ ስልጠና የተገኘ፣ ለቀጥታና ውስን ክፍያ ተጨባጭ የሆነ የምክርና ሌሎች አገልግሎት ለሌሎች የማበርከት አላማ ያለው የስራ ዘርፍ ነው። ሙያ በቀላሉ ሊተካ የማይችል ልዩ የሆነ እውቀትና ክህሎት የሚጠይቅ ሲሆን ወደ ሙያው ለመግባት የተወሰነ የመግቢያ መስፈርት ያለውና ለሌሎች ጥቅም ወይም አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አቅም ከመሆን ባሻገር ስራውን በሚመራና በሚቆጣጠር የስነምግባር ደንብ ጋር የተቆራኘ መሰረታዊ የሙያ መገለጫ ባህሪያት አሉት። የሙያ ስነ ምግባር የሚሸፍነው ግለሰባዊ፣ ተቋማዊ የሆኑ ከባለሙያው የሚጠበቁ የባህሪ ስታንዳርዶችን ነው። በአንድ እውቅና ባገኘ ሙያ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች ልዩ ሙያና እውቀትን ያበረክታሉ። ለህዝቡ ሙያዊ እውቀታቸውን ሲያበረክቱ የሚገዙበት ጉዳይ የስነ ምግባር ጉዳይ ስለሆነ ሙያዊ ስነ ምግባር እንለዋለን።

ሙያዊ ስነምግባር የመተባበር እና የመረዳዳት ባህልን፣ የስራ እና የሙያ ጥራትን፣ ውስጣዊ መተማመንን፣ ክብሩን የጠበቀ መንግስታዊ አገልግሎትን ለማጎልበት ያገለግላል። በተጨማሪም የመንግስት ሰራተኛውን አቅም ከማጎልበት ባሻገር ከተጠያቂነት ለማዳን፣ ጤናማ የስራ ግንኙነት ለመፍጠርና በጋራ የመስራት ባህልን ለማዳበር እንዲሁም ስነምግባራዊ አመራር እውን እንዲሆን ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አለው። አንድ ባለሙያ ከሚሰራበት መስሪያ ቤት ውስጥ መከተል የሚገባቸው ተቋማዊ ስነምግባር ስንል ደግሞ በአግባቡ ልንከተላቸውና ልንተገብራቸው የሚገቡ ሲሆኑ ካልፈፀምንባቸው እርምጃ የሚያስወስዱ ናቸው። ከእነዚህ ተግባራት መካከል የስራ ሰዓት ማክበር፣ ተቋማዊ የአለባበስ ስርዓት፣ የተቋሙን ሀብት በአግባቡና በስርዓት መጠቀምና በተመደብንበት የስራ መስክ ስራዎችን በአግባቡ ማከናወን የሚሉት ይገኙበታል።

በተቋማት ውስጥ ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶች ለምን ተበራከቱ በሚል ርዕስ የተደረገው ጥናት የተገኘው መረጃ “ ማንም አያውቅም (አይደርስበትም) የሚል ግላዊ እምነት፣ ሁሉም የሚያደርገው ነው አያስጠይቅም ብሎ ማመን፣ በአቋራጭ ለመበልጸግ ባለ ግላዊ ምኞት፣ ድርጊቱ መርህንና ህግን የጣሰ መሆኑን አለማወቅ፣ አዎንታዊ የሆኑ ባህሪዎችን ሊያበረታታ የሚችል ስርአት አለመኖር፣ ስነምግባራዊ አመራር አለመኖር የችግሮቹ ዋነኛ መንስኤዎች መሆናቸውን ያመላክታል። እነዚህን የግል ሙያዊም ሆነ ተቋማዊ የስነምግባር ችግሮች ለመፍታት ራስን በጥልቀት መመልከት የሚገባ ሲሆን የመጀመሪያውና ቁልፍ የመፍትሔ እርምጃ መካከል እለታዊ ስነ ምግባራዊ ቼክ ሊስትን መጠቀም ነው።

በእለታዊ ስነ ምግባራዊ ቼክ ሊስት ውስጥ በግላችን ልንመልሳቸው ከሚገቡን መሰረታዊ ጥያቄዎች መካከል የፈጸምኩት ተግባር ህጋዊ ነውን?ውሳኔዬና የፈጸምኩት ድርጊት ሚዛኑን የጠበቀ ነውን?ውሳኔዬና ድርጊቱ እኔን ምን እንዲሰማኝ አድርጎኛል? ድርጊቱ ይፋ ቢሆን ስለ ራሴ ጥሩነት ምን ይሰማኛል? ድርጊቴ በቤተሰቦቼ ፊት እንድኮራ ያደርገኛልን? የሚሉት ይገኙበታል። በዚህ መሰረት ሁሉም የፐብሊክ ሰርቪስ ባለሙያ የስነምግባር መርሆዎችና እሴቶች ተግባራዊ በማድረግ የተቋሙን ተልዕኮ ለማሳካት በትጋት እንዲሰራ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ  ሚኒስቴር ጥሪውን ያቀርባል።

በዓለማየሁ ማሞ

ምንጭ፡- የተቋሙ የሰው ሃብት ልማትና አስተዳደር የስልጠና ማንዋል

 

 

 

Please follow and like us: