ምክር ቤቱ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴርን የ9 ወር ዕቅድ አፈጻጸም ገመገመ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 22ኛ መደበኛ ስብሰባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴርን የ9 ወር ዕቅድ አፈጻጸም ገምግሟል፡፡ የምክር ቤቱን 22ኛ መደበኛ ጉባዔ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ የተከበሩ አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ በይፋ አስጀምረውታል።

የኢፌዲሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) የተቋሙን የ9 ወር ዕቅድ አፈጻጸም ያቀረቡ ሲሆን፤ በምክር ቤቱ የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም ከህዝብ የተሰበሰቡ እና በምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ወርቀሰሙ ማሞ የሚንስቴር መስርያ ቤቱን እቅድ አፈጻጸም በሚመለከት አጠቃላይ ግብረ መልስ ያቀረቡ ሲሆን፤ ተቋሙ በየክልሉ በመሄድ ያከናወናቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እንዲሁም ወጣቱን በበጎ አድራጎት ስራ ላይ በማሳተፍ የተከናወኑት አበረታች ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

ይሁንና ከተለያዩ አከባቢዎች ወደ ከተሞች በተለይም ወደ አዲስ አበባ የሚፈልሱ ዜጎች ለጎዳና ተዳዳሪነት እየተጋለጡ መሆኑንና የከተማው ነዋሪዎችም ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች እየተጋለጡ በመሆኑ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ የተለያዩ ሴክተሮችን በማቀናጀት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አሳስበዋል፡፡

ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች፣ የሴቶች ልማት ህብረት ስራ፣ የአካል ጉዳተኞች፣ የወጣቶች ስብዕና ግንባታ፣ ሴቶችን ወደ አመራርነት ማብቃት እንዲሁም የአረጋዊያን ማእከልን ማጠናከር በቀጣይ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ነው የተከበሩ ወ/ሮ ወርቀሰሙ የገለጹት፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው ለተቋሙ የሚመደበው በጀት በቂ ባይሆንም የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን እና የማህበረሰብ ክፍሎችን በማስተባበር ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ማከናወን እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡

በተለይ ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍል የተውጣጡ ከ24 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች በመሰማራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መስጠታቸውና 18 ቢሊየን ብር የሚገመት ሀብት ማዳን መቻሉን ሚንስትሯ አስረድተዋል፡፡

የጎዳና ተዳዳሪ ዜጎችን በተመለከተ ችግሩን ከምንጩ ለመግታት በተሰራው ስራ ከ90 ሺ በላይ ዜጎች ወደ ጎዳና እንዳይወጡ መታደግ ስለመቻሉ አንስተዋል፡፡

የትግራይ ክልልን ጨምሮ ግጭት ባለባቸው አከባቢ የሚገኙ ሴቶችን ለመርዳት በተሰራው ስራ ከአለም ባንክ ጋር በመተባበር ከ200 ሺ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ስለመቻሉም አንስተዋል፡፡

ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ የሴቶች፣ ህጻናት፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋዊያን እንዲሁም ደሃና ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚሰራ በመሆኑ ከመንግስት በሚበጀተው ገንዘብ ብቻ ስራዎችን ማከናወን እንደማይቻል ክብርት ሚንስትሯ ጠቁመው ምክር ቤቱ “የማህበራዊ ሀላፊነት መወጣት አዋጅ”ን አጽድቆላቸው በቀጣይ የተሻለ ስራ እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ያካሄደውን መደበኛ ጉባኤ ከመጀመሩ በፊት የምክር ቤቱ አባል ለነበሩትና በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት የተከበሩ ወ/ሮ አለሚቱ አሰፋ የህሊና ጸሎት አደርጓል፡፡

(በ አበባው ዮሴፍ)

Please follow and like us: