ሴቶች በሀገራዊ ምክክር ሂደት ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል – ፕሬዝዳንት ሳሣህለወርቅ ዘውዴ

ሴቶች በሀገራዊ ምክክር ሂደት ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የሀገረ መንግስት ግንባታው ውጤታማ እንዲሆን ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ አስታወቁ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሴቶችን ተሳትፎ ለማጉላት “ሀገራዊ ምክክር ለአንቺ፤ ስለኢትዮጵያ በአንቺ፤ ኢትዮጵያ እየመከረች ነው” በሚል መሪ ሀሳብ የምክክር መድረክ እያካሄደ ይገኛል።

ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፤ አካታች ሀገራዊ ምክክር ማካሔድ ብሔራዊ መግባባትን የመፍጠር እና ተቀራርቦ የመስራት ባህልን ለማጎልበት ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።

በብሔራዊ ምክክር ያለፉ ሀገራት በጦርነት ከሚገኝ ጊዜያዊ መፍትሔ ይልቅ ለንግግርና ምክክር ቅድሚያ በመስጠታቸው ዘላቂ ሰላምን በመፍጠር የተሻለ ኢኮኖሚ እየገነቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ እየተካሄደ የሚገኘው ሀገራዊ ምክክር የተሻለ ሀገር ለመገንባት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ስላለው ሴቶች ገንቢ ተሳትፏቸውን ለማበርከት መዘጋጀት እንደሚኖርባቸው አስገንዝብዋል።

በኢትዮጵያ በሚፈጠሩ አለመግባባቶች እና የሃሳብ ልዩነቶች ሴቶች ግንባር ቀደም የጉዳት ሰለባ መሆናቸውን አንስተዋል።

ለዚህም በሀገረ መንግስት ግንባታ የሴቶች ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ በሀገራዊ ምክክር ሂደት ላይ ወሳኝ ተሳትፏቸውን ማጉላት እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።

ስልታዊ መፍትሔን በማበጀት ረገድ ሴቶች የተሰጣቸው ተፈጥሯዊ ፀጋ የላቀ በመሆኑ ምክክሩ ላይ የሚያደርጉት ተሳትፎ ቀላል የሚባል እንዳልሆነም አብራርተዋል።

በሀገራዊ ምክክሩ ላይ የሴቶች ድምፅ ትልቅ ቦታ እንደሚሰጠው በማመን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ሴቶች የነቃ ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው  በግጭትና በሰላም እጦት ግንባር ቀደም ተጎጂዎች ሴቶች በመሆናቸው በሀገራዊ ምክክሩ በንቃት መሳተፍና ጉልህ አስተዋጾዖ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ እውን እንዲሆን የሴቶች ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ሴቶች የተሟላና ትርጉም ያለው  ተሳትፎ እንዲኖራቸው የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸዋል ።

ከሀገሪቱ 50 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ከቤተሰብ እስከ ሀገር የሚያበረክቱት አስተዋጽዖ  ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው በየደረጃው ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ክቡር ፕሮፌሰር መሰፍን አርአያ ኮሚሽኑ በቆይታው በርካታ አበረታች ሥራዎችን እየሰራ ቢሆንም ከሴቶች ተሳትፎ አኳያ መጠናከር አለበት ብለዋል።

በመድረኩ በኮሚሽኑ እስካሁን የተሰሩ ስራዎች፣ በሂደቱ የሴቶችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እንዲሁም በዚህ ረገድ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ተዳሷል።
እንዲሁም ሀገራዊ ምክክሩ የሴቶችን ተሳትፎና ሚና ማሳደግ በሚቻልበት አግባብ ላይ የፖናል ውይይት ተካሂዷል።

በመድረኩ ከፌዴራልና ከክልል የመንግስት አካላት እና ከሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች የተውጣጡ ሴቶች እየተሳተፉ ይገኛል።

 

Please follow and like us: