ወላጆቻቸውን ያጡና ለችግር የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን በተቀናጀና ዘላቂነት ባለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመደገፍ የመንግስትና ሲቪክ ተቋማት ከበጎ ፈቃደኞች ጋር ተቀናጅተው በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ገለጹ

‘ለሀገራዊ ችግሮች ሀገራዊ መፍትሔ’ በሚል መርህ ወላጆቻቸውን ያጡና ለችግር የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን በተቀናጀና ዘላቂነት ባለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመደገፍ የመንግስትና ሲቪክ ተቋማት ከበጎ ፈቃደኞች ጋር ተቀናጅተው በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ገለጹ። ይህ የተገለጸው የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አሊያንስ ኬር ናው/Alliance Care Now (ANC)/ ከተባለ በጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመተባበር ወላጆቻቸውን ያጡና ለችግር የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ የተፈረመውን የፕሮጀክት ስምምነት ለመተግበር እንዲያስችል በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋመው የበጎ ፈቃድ ብሔራዊ ስትሪንግ ኮሚቴ ውይይት በማካሄደበት ወቅት ነው።

በውይይቱ ላይ የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንዳሉት፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ወላጆቻቸውን ያጡና ለችግር የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍና ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን ከተለያዩ ባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በመተባበር እያከናወነ ይገኛል ብለዋል። በአማራጭ የህጻናት የድጋፍና ክብካቤ ፕሮግራም እና በከተማና የገጠር ሴፍቲኔት ፕሮግራም ዜጎችን ለመደገፍ ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል። የበጎ ፈቃድ ስራ ወቅት ጠብቆ በሚካሄድ የዘመቻ ስራ ብቻ ታጥሮ እንዳይቀር ይልቁንም ዘላቂና ቀጣይነት እንዲኖረው በስርዓት መደገፍ አለበት ያሉት ሚኒስትሯ የበጎ ፈቃድ ስራ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፖሊሲ እና የዜግነት አገልግሎት ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱንና ጸድቆ በስራ ላይ እንዲውልም ለሚመለከተው አካል መቅረቡን ገልጸዋል። በተመሳሳይ በተለያየ አግባብ የበጎ ፈቃድ ስራዎችን በግልም ሆነ በጋራ መስራት ለሚፈልግ ማንኛውም አካል መረጃ ለመስጠትና የተሰሩ ስራዎችንም ለማደራጀት የሚረዳ የመረጃ ስርዓት መዘርጋቱንና በየደረጃው ውይይት እየተካሄደበት መሆኑንም አያይዘው ጠቁመዋል። ሆኖም በተለያዩ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ክስተቶች ሳቢያ ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናትን ጨምሮ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮች የተጋለጡ ወገኖችን ይበልጥ ተደራሽና ተጠቃሚ ለማድረግ በመንግስት፣ በሲቪክ ተቋማትና በበጎ ፈቃደኞች መካከል ጠንካራ ጥምረት ፈጥሮ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ብለዋል።

ከዚህ አኳያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቀደም ሲልም ከአሊያንስ ኬር ናው እና ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋሟት ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈረሙን አስታውሰዋል። በአሁኑ ወቅትም ፕሮግራሙ ሀገራዊ ይዘት እንዲኖረው ለማስቻል በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።በቀጣይም በተለይ የህጻናት ድጋፍና ክብካቤ፣ የሀገር ውስጥ ጉዲፈቻንና ልዩ ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ጉዳይ ተቋሙ በሚተገበረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፕሮግራም ወስጥ በማካተት ተፈጻሚ ያደርጋል ብለዋል።በሌሎችም ሀገራዊ ፕሮግራሞችና በተቋማት ዘንድ ትኩረት እንዲሰጠው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የበኩሉን እንደሚወጣ ሚንስትሯ ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገልጸዋል። ተቋማትም የእቅዳቸው አካል በማድረግ ለተፈጻሚነቱ በቁርጠኝነት እንዲረባረቡም ጥሪ አቅርበዋል። በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የማህበራዊ ክላስተር ሰብሳቢ አቶ በቀለ መንገሻ በበኩላቸው የበጎ ፈቃድ ስራ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ጭምር ኢኒሼቲቭ መሆኑን እና እንደሀገርም ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል። ዘርፉ ከማህበራዊ ግልጋሎት ባለፈ የኢኮኖሚ ችግሮችን ለመቅረፍ፣ የእርስ በእርስ ግንኙነትን ለማጠናከር፣ የበጎነት እሴቶችን ለማጎልበት እንዲሁም የሀገር ስብራትን ለመጠገን ብሎም ለሀገር እድገትና ለገጽታ ግንባታ ጉልህ አስተዋጽዖ ስለሚያበረክት ፕሮግራሙ በስርዓት እንዲደገፍና ውጤታማ እንዲሆን ጽ/ቤቱ የክትትል ስራ እንደሚሰራና አስፈላጊውንም ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

የአሊያንስ ኬርናው መስራችና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ናሆሚ ሀይሌ ፕሮግራሙ ቀደም ሲል በፖይለት ደረጃ ሲተገበር መቆየቱንና ውጤታማ እንደነበር ተናግረዋል።ፕሮግራሙ በሰባት ዘርፎች በዋናነትም የሀገር ውስጥ ጉዲፈቻን ማስፋፋት፣ የማጠናከሪያ ትምህርት ድጋፍ፣ የሳተላይት የጤና ህክምና ክሊኒክ ድጋፍ፣ የህይወት ክህሎት ስልጠና፣ መጠለያ ለሌላቸው እናቶች የህጻናት እንክብካቤ፣ ልዩ ድጋፍ ለሚሹ ድጋፍ ማድረግን እንደሚያካትት እና በቀጣይ አምስት አመታት ከበጎ ፈቃድ ስራ ጋር በማስተሳሰር በየደረጃው እንደሚተገበር ተገልጿል። ፕሮግራሙ ተጋላጭ ወገኖችን ችግር ለመቅረፍና ለመደገፍ የሚያስችል ጠንካራ ስርዓት ከመዘርጋት አኳያ በመንግስት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን ይበልጥ ለማጠናከርና ውጤታማ ለማድረግ ያለመ ነው ተብሏል። በውይይቱ ተሳታፊዎች በየተቋማቸው ያለውን ተሞክሮ ያካፈሉ ሲሆን በቀጣይም ከተቋማቸው እቅድ ጋር አስተሳስረው ለመተግበር፣ የዜጎችን ችግር ለመቅረፍና ተጠቃሚ ለማድረግ ከበጎ ፈቃደኞች ጋር ተቀናጅተው በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። በውይይቱ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከአሊያንስ ኬር ናው እንዲሁም ከፌዴራል ተቋማት፣ ሲቪክ ድርጅቶች፣ ከክልልና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ተወካዮች ተገኝተዋል።

 

Please follow and like us: