የተቋሙ ሰራተኞች ለተሻለ ተቋማዊ አፈጻጸምና ስኬት በላቀ ትጋትና ተነሳሽነት ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ

የተቋሙ ሰራተኞች ለተሻለ ተቋማዊ አፈጻጸምና ስኬት በላቀ ትጋትና ተነሳሽነት ሊሰሩ እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ አመራር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ እሸቱ ገለጹ። ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሰራተኞች በአመለካከትና አስተሳሰስ ለውጥ (Mindset) ላይ ያተኮረ የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል።

በስልጠና መርሀ ግብሩ ላይ የሚኒስቴሩ ስራ አመራር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ እሸቱ እንደተናገሩት፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተቋሙ ተደራሽ የሆኑትን የህብረተሰብ ክፍሎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመዋል። ሆኖም ተቋሙ ሰፊ ኃላፊነት የተጣለበት፥ ለዜጎችም ሰፊ አገልግሎት መስጠት የሚጠበቅበት በመሆኑ በየዘርፉ የተቀመጡ ግቦችን እንዲሳኩ ብዙ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ለዚህም የተቋሙ ሰራተኞች በየተሰማሩበት ዘርፍ የአገልጋይነትን ስሜት በመላበስ በላቀ ትጋትና ተነሳሽነት ሊሰሩ እንደሚገባ ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ ሙሉጌታ እሸቱ ገልጸዋል። በአመለካከትም ሆነ በተግባር የተለወጠ ብሎም ያለውን እውቀትና ክህሎት በሚገባ መጠቀም የሚችል የሰው ሃይል ማፍራት ያስፈልጋል ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፥ የአቅም ግንባታ ስልጠናው መዘጋጀቱም ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል።

 

Please follow and like us: