የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር በመተባበር የትንሳዔ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለአረጋውያን ማዕድ አጋሩ

የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር በመተባበር የ2016 የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግ ሰሚት ሰንሻይን ፊላንትሮፒ ፋውንዴሽን የአረጋውያን መጦሪያና መንከባከቢያ ማዕከል ለሚኖሩ አረጋውያን ማዕድ አጋርተዋል::

የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ዛሬ የቆምነው ትናንት አረጋውያን በሰሩት ስራ ላይ በመሆኑ የሀገር ባለውለታ አረጋውያን እና ጧሪ ደጋፊ የሌላቸው አቅመ ደካሞችን መደገፍና መንከባከብ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆን እንዳለበት ተናግረዋል። የቱንም ያህል ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ቢበዙብንም እኛ ኢትዮጵያውያን ኩሩ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህል ያለን ጠንካራ ህዝቦች በመሆናችን ይህን በጎ እሴት ይበልጥ ማጎልበት ይኖርብናል ብለዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችንና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አቅመ ደካማ ወገኖችን ለመደገፍና በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ለማስቻል በርካታ ስራዎችን በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በቀጣይም ባለድርሻና አጋር አካላትን በማስተባበር ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። ሰንሻይን ኮንስትራክሸን ኢንቨስትመንት ግሩፕ አረጋውያንን ተጠቃሚ ለማደረግ እያከናወነ ያለውን ተግባራትን አድንቀዋል፤ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና በአረጋውያን ስም አመስግነው።

የትንሳኤ በዓል ሲከበርም ህብረተሰቡ፣ ባሃብቶችና የበጎ አድራጎት ተቋማት የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት፣ በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ በማድረግና ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት እንዲሆን ሚኒስትሯ ጥሪ አቅርበዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደሰ ዳባ በበኩላቸው ጤና ሚኒስቴር የህብረተሰቡን ጤና ለማስጠበቅ ትልቅ ኃላፊነት የተጣለበት በመሆኑ የጤና አገልግሎትን ተደራሸ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። አረጋውያንን መደገፍና አብሮ መዋል፥ መንከባከብና  ፍቅር መስጠት ትልቅ ጸጋና መባረክ ነው ብለዋል። ጤና ሚኒስቴር ወደፊትም ከፋውንዴሽኑ ጋር በጋራ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

ሰንሻይን ኮንስትራክሸን ኢንቨስትመንት ግሩፕ መስራችና ባለቤት ክቡር ዶ/ር ሳሙኤል ታፈሰ ከበዓል ወቅት ባሻገር እያከናወነ ያለውን የበጎ አድራጎት ስራ ወደፊትም አጠናክሮ እንደሚቀጥልና ማህበራዊ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ገልጸዋል። በፕሮግራሙ ላይ አረጋውያንን ጨምሮ የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደሰ ዳባ፣ የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሙና አህመድ እንዲሁም የሰንሻይን ፍላንትሮፒ ፋውንዴሽን የስራ ኃላፊዎችና ባልደረቦች ተገኝተዋል።

ማዕከሉ እስከ 750 ለሚሆኑ አረጋውያን የመጠለያ፣ የገቢ ማስገኛ፣ የቤተመጽሃፍት፣ የህክምና፣ የእደ- ጥበብ፣ የላውንደሪና ሌሎችም ሁለገብ አገልግሎት የመስጠት አቅም እንዳለው በጉብኝት ወቅት ተገልጿል።

 

Please follow and like us: