በሀገር አቀፍ ደረጃ ለህፃናት ሁለንተናዊ ደህንነትና ሌሎች ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የማህበራዊ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ባለሙያዎች ያሉበትን አጠቃላይ ሁኔታ የሚያሳይ የዳሰሳ ጥናት እንደሚካሄድ ተገለጸ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በአፋር ክልል የዳሰሳ ጥናቱን ለማካሄድ እንዲያስችል በመረጃ አሰባሰብ ሂደት የሚሰማሩ ባለሙያዎቸን አቅም ለማጎልበት ያለመ የሥልጠና መድረክ አዘጋጅቷል።

በመድረኩ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የማህበራዊ ጥበቃ ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ዴስክ ኃላፊ የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ሹመት ባስተላለፉት መልዕክት፥ የማህበራዊ እድገትን ለማስቀጠል መንግስት የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲን ጨምሮ በርካታ የአሰራር ማዕቀፎችን በማውጣትና ፕሮግራሞችን በመዘርጋት የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።ሆኖም ውጤታማና የተጠናከረ የማህበራዊ ጥበቃ ሥርዓት ለመዘርጋትና አገልግሎቱን በየደረጃው ላለው የህብረተሰብ ክፍል በአግባቡ ተደራሽ ለማድረግ መዋቅሩን እስከታችኛው የአስተዳደር ዕርከን ድረስ መዘርጋት እና በበቂ የሰው ሃይል ማደራጀት አስፈላጊው መሆኑን ተናግረዋል። በዚህ መነሻነት የማህበራዊ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ባለሙያዎች ያሉበትን አጠቃላይ ሁኔታ የሚያሳይ (Social services workforce mapping and assessment) የዳሰሳ ጥናት በሀገር አቀፍ ደረጃ እንደሚካሄድ ገልጸዋል። የዳሰሳ ጥናቱ በአይነቱ የመጀመሪያ እንደሆነ የጠቁሙት ዴስክ ኃላፊው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ጨምሮ በተዋረድ ባሉ አደረጃጀቶች እንዲሁም ሌሎች የሴክተር መ/ቤቶች እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ወስጥ ተቀጥረው ለህፃናት ሁለንተናዊ ደህንነት ብሎም ሌሎች ድሃና ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ የማህበራዊ ባለሙያዎችን ነባራዊ ሁኔታ ይዳስሳል ብለዋል፡፡

የዳሰሳ ጥናቱ ከአፋር ክልል በተጨማሪ በቀሪዎቹ ክልሎችና የከተማ አስተዳድሮችም ደረጃ በደረጃ ለማካሄድ ዕቅድ መያዙንና ዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ለዳሰሳ ጥናቱ የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል። የአፋር ብ/ከ/መ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ፋጡማ መሀመድ ያሲን በበኩላቸው የሚካሄደው የዳሰሳ ጥናት ክልሉ አሁን ላይ ያሉትን የማህበራዊ ባለሙያዎች የተጠናከረ መረጃ እንዲኖረው ከማድረጉም ባሻገር በቀጣይ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ያለውን የሰው ሃይል ለማጠናከር ለሚወሰደው እርምጃ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደርጋል ብለዋል።

Please follow and like us: